Sunday, April 4, 2010

ተነሥቶአል


ፍርሃት የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ገባ ከድኖታል። ምንም እንኳ የፋሲካ ሰንበት ማለትም እስራኤላውያን ከባርነት ነጻ የወጡበት መታሰቢያ የሚከበርበት ቢሆንም ከሳምንት በፊት የነበረው ስሜት የለም። ከሳምንት በፊት መሲሁ ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቱና በውርጫው ላይ ተቀምጦ ሲገባ፥ ሕዝቡ በሙሉ ሆሳዕና በአርያም እያለ ነበር የተቀበለው፤ አሁን ግን ያ ሁሉ የለም፤ ያ ለህዝቡ የመጣው አዳኝ ተይዞ ተገርፎ ተዘብቶበት ተሰቅሎአል። መሰቀል ብቻ አይደለም ተቀብሮአል፤ ለዚያውም በእንግዶች መቃብር።
ጊዜው ለርሱ ተከታዮች አስቸጋሪ ነበር። ይሁዳ ሸጠው፥ ጴጥሮስ ካደው፥ ማርቆስ  ራቁቱን እስኪቀር ድረስ ልብሱን ጥሎ ሸሸ። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ተበተኑ። ገሚሶቹ ወደ ቀደመ ተግባራቸው ማለትም አሳ ወደ ማጥመዱ፥ ወደ ቀረጡ፥ ገሚሶቹ በፍርሃት ተሸብበው በዝግ ቤት ተቀመጡ።
በሥውር ደቀ መዛሙርት የነበሩት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ጲላጦስን ለምነው የጌታን መቃብር ገነዙት፥ በአዲስ መቃብር ቀበሩት ፤ አባቶቻችን በትውፊት እንደነገሩን ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል የማይሞት የማይለወጥ እያሉ ገነዙት፤
የካህናት አለቆች እንደተሳካላቸው ቆጥረው በደስታ ሰከሩ፤ ሥጋውን ለማስጠበቅም በመቃብሩ ላይ ወታደሮችን አቆሙ።
ነገር ግን የፈሪሳውያን ጠንቃቃነት፥ የወታደሮቹ ጀግንነት የዘመናትን ምኞት፥የነቢያትን ትንቢት፥ የሱባዔውን ፍጻሜ ሊገታ አልቻለውም። ማህተመ ድንግልናዋን ሳይለውጥ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተለወለደው ጌታ በዚያ በመንፈቀ ሌሊት መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ተነሣ።
ሞት የገዛውና የሞት ምርኮኛ የነበረው  የአዳም የተስፋው ፍጻሜ ከሞት ተነሣ። በክስ ወደ እግዚአብሔር ከሚጮኸው ከአቤል ደም ይልቅ የአዳምን ልጆች ኃጢአት የሚያነጻው ከሞት ተነሣ። አብርሃም በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ ያየው በግ የይስሐቅ ቤዛና ምትክ ለአብርሃም ልጆች ቤዛ ሊሆን ከሞት ተነሥቶአል።
ሀ ላንቀላፉት በኩር ሆኖ ተነስቶአል
ከሞት የተነሱ ብዙ ናቸው፤ ወለተ ኢያኢሮስ ከሙታን ተሰታለች። አልአዛር ከሞት ተነሥቶአል። ቀድሞም በብሉይ ኪዳን ብዙዎች ከሞት ተነሥተዋል። የክርስቶስን ሞት ከሌሌቹ የሚለየው በምንድነው ብሎ የሚጠይቅ ቢኖር፥ ምንም እንኳ
ሌሎቹ ከሞት ቢነሡም፥ የተነሡት ሞት በሚገዛው ሥጋቸው ስለሆነ ተመልሰው ሞተዋል። ክርስቶስ የተነሣው ሞት ለገዛን በሙሉ በእንዴት ያለ አኳኋን እንደምንነሳ ምሳሌ ሆኖን ነው የተነሣው። ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የክርስቶስ ትንሣኤን ትርጉም በተናገረበት አንቀጽ
አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በሰው በኩል ስለ መጣ ትንሣኤ ሙታን በሰው በኩል ሆኖአልና። ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ደግሞ ሕያዋን ይሆናሉና።   15 23 ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ ክርስቶስ እንደ በኩራት ነው፥ በኋላም በመምጣቱ ለክርስቶስ የሆኑት ናቸው፤
በማለት የክርስቶስ ትንሣኤ ሞትን ድል ያደረገ በአዳም በኩል ወደ ሰው ልጆች የመጣውን የሞት ፍርድ ያስወገደና በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን የሙታን ትንሣኤ ያስረገጠ እንደሆነ በመግለጥ ይህ የክርስትናችን ታላቅ ተስፋ እንደሆነ ገልጦአል፤ 1 ቆሮ 15፥21-23።  

ቅዱስ ጴጥሮስም ይህ የክርስቶስ ትንሣኤ የዘመናት ምኞት የተፈጸመበት እንደሆነ ለማመልከት ቅዱስ ዳዊት ከብዙ ዘመን በፊት የተነበየውን ትንቢት በማውሳት የዳዊት ትንቢት የተፈጸመው በክርስቶስ እንደሆነ ይገልጥልናል።  
የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤   እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና። ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፥ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና።  ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፥ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፥ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም። የሕይወትን መንገድ አስታወቅኸኝ፤ ከፊትህ ጋር ደስታን ትሞላብኛለህ።
ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት እንደ ሞተም እንደ ተቀበረም ለእናንተ በግልጥ እናገር ዘንድ ፍቀዱልኝ፤ መቃብሩም እስከ ዛሬ በእኛ ዘንድ ነው። ነቢይ ስለ ሆነ፥ ከወገቡም ፍሬ በዙፋኑ ያስቀምጥ ዘንድ እግዚአብሔር መሐላ እንደ ማለለት ስለ አወቀ፥  ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ አስቀድሞ አይቶ፥ ነፍሱ በሲኦል እንዳልቀረች ሥጋውም መበስበስን እንዳላየ ተናገረ። ይህን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው ለዚህም ነገር እኛ ሁላችን ምስክሮች ነን፤ ሐዋ 2፥22-32
ይህ የጴጥሮስ ስብከት በዚህ ዘመን ለምንኖር በሙሉ ታላቅ መልእክት ያለው ነው። ሐዋርያው የሚለን ዳዊት << ሥጋዬ በተስፋ ያድራል>> በማለት በመንፈስ ቅዱስ ተመልቶ የተናገረው፥ የክርስቶስን ትንሣኤ ከሩቅ ተመልክቶ ነው። ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ምክንያት ለዘላለም ህይወት ለዘላለም ሕይወት ተስፋ አለኝ አለ።
ይህ የዳዊት ተስፋ የእኛም  ተስፋ ነው። ከንቱ ሆነን የምንቀር አይደለንም። ለኑሮአችን ትንሣኤ አለው። ለሞተው ነገራችን ትንሣኤ አለው። አለቀ አበቃ ደቀቀ ለምንለው ነገር ትንሣኤ አለው። ትንሣኤው በሞትና በመውጊያው በኃጢአት ላይ ድል አድራጊነትን ስላጎናጸፈን ዛሬ እኛም ከጴጥሮስ ጋር፥ እኛም ከዳዊት ጋር ሆነን << ሥጋዬ በተስፋ ያድራል>> እንላለን። ከጳውሎስ ጋር ሆነንም በታላቅ ድምጽ ያገኘነውን ድል እንናገራለን። እንዲህም እያልን፤
ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?   የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው፤   ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠንለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
1 ቆሮ 15 55-57

No comments:

Post a Comment