Tuesday, May 29, 2012

ክፍል ሁለት ሕይወትን የሚለውጥ መልእክት 1:11-2:21



ይህን ከመጀመራችን በፊት ራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን ነገር ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቴ ያለው ቦታ ምን ያህል ነው:: የክርስቶስ ወንጌል ሕይወቴን ምን ያህል ለውጦታል? ይህን የእግዚአብሔርን ቃል መማሬ በተግባሬ በኑሮዬ አካሄድ እና እርምጃ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ አምጥቶአል? ክርስትና የለውጥ ሃይማኖት ነው:: በመሆኑም ቅዱስ ጳውሎስ በሚገርም ሁኔታ የእርሱን ሕይወት በጥንቃቄ እንድንመለከት ይነግረናል:: ገላትያ 4:12:: 1ቆሮ 4:16:: 11:1:: ፊል 3:17:: 4:8-9:: 

ሀ. ጳውሎስ የጸጋውን ወንጌል በቀጥታ ከጌታ ስለመቀበሉ:: 1:10-12
ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤12 ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም።
1. ጳውሎስ ወንጌሉን የሰበከው በሰዋዊ መንገድ አይደለም። 
2. ጳውሎስ ወንጌሉን  ከሰው አልተማረውም ወይም አልተቀበለውም።
<< እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም>>


ለ. የጳውሎስ የቀደመው የይሁዲነት ሕይወት ለጸጋው ወንጌል መነሻ አለመሆኑ 1:13-14
በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥14 ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።

ሐ. ጳውሎስ ወንጌሉን የተቀበለው ከሰው አይደለም:: 1:15-24:: 
በቍጥር 11-12 ላይ የጀመረውን ወንጌሉን በትምህርትና በሰው ትውፊት እንዳልተቀበለው ይልቁኑም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገለጠለትና ይህንንም ወንጌል ለማስተማር ሲነሳ ከማንም ሰው ጋር እንዳልተመካከረ በመግለጥ የእርሱ ወደ ክርስትና መግባት በይሁዳ ባሉት አብያተ ክርስቲያናት (ማኅበሮች) መካከል እንዴት አድናቆትን እንደፈጠረ ይነግረናል:: 

1. እግዚአብሔር የክርስቶስን የጸጋ ወንጌል ለጳውሎስ የገለጠበት ሁኔታ
 ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥

2. ጳውሎስ ከሐዋርያት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘበት ሁኔታ 
ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። 18 ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤19 ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። 20 ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።21 ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። 22 በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ 23 ነገር ግን ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ 24 ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።

መ. ጳውሎስ የሰበከው ወንጌል በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ተቀባይነት ስለማግኘቱ 2:1-10
በዚህ ክፍል ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ ያስተማረውን ወንጌልና የሐዋርያነቱን ተልዕኮ ከተቀበለ በኋላ ለሚቀጥሉት 14 ዓመታት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደነበረ ይገልጥልናል:: በዚህ ክፍል ቅዱስ ጳውሎስ  ከአሥራ አራት አመት በኋላ እንደገና ከሐዋርያት ጋር ሲገናኝ የነበረውን ሁኔታ እናያለን:: በአስራ አራተኛ ዓመት በኋላ የሚለው የትኛውን ነው? ወደክርስትና ከገባ በኋላ ነው ወይስ ከመጀመሪያው የኢየሩሳሌም ጉብኝት በኋላ ነው ለሚለው በሊቃውንቱ መካከል የተለያየ አስተያየት አለ:: አብዛኛው ሊቃውንት የሚስማሙበት ይህ አስራ አራት ዓመት ጳውሎስ ወደ ክርስትና ከገባ በኋላ ጀምሮ ያለውን ነው::  
የጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ 
መነሻ                ቀን             ማስረጃ                     ትይዩ                     ምክንያት  
ደማስቆ             35                  9:22-30             ገላ1:18-24          ጴጥሮስን ለማነጋገር 
የሶርያ አንጾኪያ   46            11:30;12:25          ገላ 2:1-3,6-10    ለድሆች እርዳታ
                                                                                                     የአሕዛብ ጉዳይ 
የሶርያ አንጾኪያ   49            14:26-15:29                                    የአሕዛብ ወደ ክርስትና       
                                                                                                      መግባት
ቆሮንቶስ            52             18:1,18,22                                         የፋሲካ በአል
                                                                                                      የድሆች እርዳታ 
ግሪክ                57             20:2-3;21:17                                       ለድሆች እርዳታ 
                                       ሮሜ15:25-31

1.ጳውሎስ ከበርናባስና ከቲቶ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ:: 
1ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤2 እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ 
በርናባስ በአገልግሎቱ << የመጽናናት ልጅ>> ተብሎ በሐዋርያት የተጠራ (ሐዋ ሥራ 4:36) የማርቆስ አጎት (ቆላ 4:10) ነው:: ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዙ እና ሰዎችን በማበረታታትና በማጽናት ለአገልግሎት ማብቃቱ እና በመንፈስ ቅዱስ መመራቱ  በሁሉም ዘንድ የታወቀለት ሐዋርያ ነው:: ሐዋ 4:36-37:: 9:26-30:: 11:22-26:: በሐዋርያነት ከጳውሎስ ጋር በአንድነት ያገለገለ ነው:: 14:14::15:12,25::  በዚሁ በገላትያ መልእክት በምናገኘው በጴጥሮስ ድርጊትና እና በሁለተኛው ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት በማርቆስ ምክንያት ጳውሎስ እና በርናባስ ተጋጭተዋል:: (ገላ 2:11-21:: ሐዋ ሥራ 15:39-40::) ሆኖም ይህ ግጭት በስተመጨረሻ በእርቅ ተቋጭቶአል:: 1ቆሮ 9:6:: ሁለተኛ ከበርናባስ ጋር ይዞ የወጣው ቲቶን ነው:: ቲቶ ጳውሎስ ወደ ክርስትና ካመጣቸው የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አንዱ እና በመንፈሳዊ ሕይወቱና በክርስትና እውቀቱ ለታላቅ የመሪነት አገልግሎት የበቃ ነው::  ቲቶ 1:4:: 
2. ጳውሎስ የሚሰብከውን ወንጌል ገለጠላቸው:: 
ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው።

3. የኢየሩሳሌም መሪዎች ቲቶ ይገረዝ ዘንድ አላስገደዱትም:: 
3ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤ 

4. ሐሰተኞች ወንድሞች ወደ ኦሪት ባርነት ሊያስገቡዋቸው ሞከሩ:: 
ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ።5 የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።

5. ሐዋርያት ጳውሎስ ለሚሰብከው ወንጌል አንድነታቸውን ገለጡ:: 
6አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥7ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤8 ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። 9ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤10 ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።

ሠ. ጳውሎስ ኬፋን (ጴጥሮስን) ስለመገሰጹ 2:11-14
ይህ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መገኘቱ ቅዱሱ መጽሐፋችን ምን ያህል የእውነት መጽሐፍ እንደሆነ የሚያሳየን ነው:: የሙሴ አለመታዘዝ የዳዊት በኃጢአት መውደቅ የጴጥሮስ ክህደት እንደተመዘገበበት ሁሉ በዚህም ቦታ በሁለት ወይም በርናባስን ከጨመርን በሦስት ታላላቅ መምህራን መካከል የተፈጠረውን ግጭት እና ይህም ለምን እንደሆነ እናያለን:: 

11 ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና።12 አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። 13 የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። 14 ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን። አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት። 

ረ.  በሥራ ሳይሆን በእምነት ስለሚሆን ጽድቅ 2:15-21
ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ራሱ ሕይወት በመመለስ በአይሁዳዊነቱ የጽድቁ መሠረት የሆነው አይሁድነቱ ሳይሆን በክርስቶስ ማመኑ እንደሆነና ይህም ለምን እንደሆነ ያብራራልና:: 
1. የጽድቃችን መሠረት በክርስቶስ ማመናችን ነው:: 
15 እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤ 16 ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል። 
2. በክርስቶስ በማመን መጽደቅ ማለት ምን ማለት ነው? 
17 ነገር ግን በክርስቶስ ልንጸድቅ የምንፈልግ ስንሆን ራሳችን ደግሞ ኃጢአተኞች ሆነን ከተገኘን፥ እንግዲያስ ክርስቶስ የኃጢአት አገልጋይ ነዋ? አይደለም። 18 ያፈረስሁትን ይህን እንደ ገና የማንጽ ከሆንሁ ራሴ ሕግ ተላላፊ እንድሆን አስረዳለሁና።19 እኔ ለእግዚአብሔር ሕያው ሆኜ እኖር ዘንድ በሕግ በኩል ለሕግ ሞቼ ነበርና። 20 ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፤ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው። 21 የእግዚአብሔርን ጸጋ አልጥልም፤ ጽድቅስ በሕግ በኩል ከሆነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ።
1. በክርስቶስ በማመን ጸድቀናል በክርስቶስ መንፈስ እንመራለን ማለት ነው:: 

2. በክርስቶስ በማመን ጽደቀናል ማለት ከክርስቶስ ጋር ተሰቅለናል ማለት ነው:: 

3. በክርስቶስ በማመን ጽድቀናል ማለት ክርስቶስ በእኛ ይኖራል ማለት ነው:: 

3 comments:

  1. Great work yesterday!
    Question: You advised yesterday to focus on one thing in our lives (as Paul did on spreading the Gospel) and never to let go and keep working at it.
    I have been asking God through prayer what my call in my life is for quite a while now. I don't believe I heard back because I end up thinking about multiple things I would like to do though my preference is to focus on the one thing.
    How do I know to focus on the one thing God wants me to focus on? Overall, how do you hear from God and discern his ways for how our lives need to be led?
    Thanks!
    P.S. You can reply in Amharic. I don't have the Amharic software to ask in Amharic. :)

    Anonymous from Seattle.

    ReplyDelete
  2. የተወደዱ አስተያየት ሰጪ እግዚአብሔር ያክብርልኝ ስለ አስተያየትዎ:: እንዳሉትም ብዙዎች እንዲጠቀሙበት መልሴን አጠር አድርጌ በአማርኛ እሰጣለሁ:: አጠር አድርጌ ያልኩበት ምክንያት በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በሰፊው ለመጻፍ ስለምፈልግ ነው::
    ብዙ ጊዜ በሕይወታችን ፈቃደ እግዚአብሔርን ስለመፈለግ ስናስብ ሦስት ነገሮችን ማሰብ አለብን:: አንደኛው አይምሰለን እንጂ ወደ ዚህ ምድር ከመጣንበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እግዚአብሔር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መርቶናል:: ማለትም የሕይወት ልምምዳችን ታላቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የምንማርበት መንገዳችን ነው:: ስኬታማ የሆንባቸው ወይም እውነተኛ የልብ ደስታ ያገኘንባቸው ወይም ደግሞ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ለውጥ በሰውም ሆነ በራሳችን ላይ ያመጣንባቸው የሕይወት ተሞክሮአችን የትኞቹ ናቸው? እነዚህን ረጋ ብሎ ማየት ብዙ ነገርን እንድንማርና በዚያ ውስጥ ከዚህ በፊት ያላየናቸውን የሕይወት አሻራዎች ልንመለከት እንችላለን::

    ሁለተኛው እግዚአብሔር የሚከፍትልን በርና የሚሰጠን ሰው ነው:: ዕድሎች ስጦቻዎቻችን የምንገልጥባቸው መድረኮች ናቸው:: የተለያዩ በሮችን ማንኳኳት ፈቃደ እግዚአብሔርን እንዳለማግኘት ልናየው አይገባም:: በጳውሎስ ሕይወት እንዳየነው በወንጌል አገልግሎቱ ውስጥ ሁልጊዜ ስለበሮችና (እድሎችና) ስለሰዎች ይናገራል:: በርናባስ ሲልውያኖስ (ሲላስ) ማርቆስ ፌቤን ወዘተ የጳውሎስ የትኩረቱ ደጋፊዎች ናቸው:: እነዚህ የጳውሎስን አገልግሎትና ትኩረት መልክ እንዲኖረው የረዱ ሰዎች ናቸው እንጂ ሁሉ ነገር ከተከናወነ በኋላ የመጡ አይደሉም:: በማን ተጽዕኖ ሥር ነን? ከማን ጋር ነው የምንውለው? ብዙ ጊዜስ የምንሞክራቸው ነገሮች ምን ዓይነት ናቸው?

    ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምንም እንኳ አንድ ነገር ላይ በዋናነት እንበል እንጂ ያ ዋና ነገር ታላቅ ሰሌዳ ነው:: በውስጡ ግን ብዙ ንድፎች ይኖራሉ:: በቅዱስ ጳውሎስ አገልግሎት ውስጥ ለምሳሌ ወንጌልን ለአሕዛብ ለማዳረስ የሚለው ታላቁ ሰሌዳ ይሁን እንጂ በውስጡ ብዙ ጥቃቅን ንድፎች ነበሩ::
    የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ማጽናት (ገላትያን ለመጻፍ የደከመው በዚህ ምክንያት ነው::) በኢየሩሳሌም ያሉትን ድሆችን መርዳት እንዲሁም ወደክርስትና የገቡትን አሳድጎ ለአገልግሎት ማብቃት ዋና ዋናዎቹ የጳውሎስን አትኩሮት የያዙ ነበሩ:: ወደኛ ነገር ስንመጣ አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን እግዚአብሔር ጥቃቅኑን ንድፍ ሊያሳየን ይችላል:: ትልቁ ሰሌዳ (ሥዕል) ወደኋላ ሊመጣ ይችላል:: እነዚህን ነገሮች አንዳንዶቹ ምናልባትም በዓይናችን ፊት የማይሞሉ ወይም ከታላቁ ሥዕል ጋር አብረው የማይያዙ መስለው ሊታዩን ይችላሉ:: ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ ድንኳን ሰፊ ነበር:: ከወንጌል አገልግሎቱ ጋር ምን ተያያዥነት አለው? በአንድ በኩል አገልግሎቱን በነጻነት ያለምንም ፋይናንሺያል ጥገኝነት እንዲያከናውን አድርጎታል:: በሌላ በኩል ደግሞ በሙያው ተሳታፊ የሆኑ የወንጌል ሰዎችን (አቂላና ጵርስቅላን) እንዲገናኝ አድርጎታል::

    እነዚህን እንደመነሻ አሳቦች ከወሰደን ወደፊት እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር ስለሕይወት ጥሪያችን ከእግዚአብሔር ቃልና ከመንፈሳዊ ሕይወት አንጻር ሰፋ አድርጌ እጽፋለሁ:: ለአስተያየት ሰጪዬም እግዚአብሔር አምላክ ክብሩን ገልጦ ፈቃዱን ያስታውቅልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን
    ቀሲስ መልአኩ::

    ReplyDelete
  3. Lord bless you. you have revealed the truth. thank you I will read it again

    ReplyDelete