እጅግ ደስ ከሚያሰኙኝ የልጅነት ትዝታዎቼ መካከል፥ በዕለተ ሰንበት ከወላጅ አባቴ ጋር በመሆን ወደቤተ ክርስቲያን በመሄድ አብሬያቸው የሰናብቱን መዝሙር መቆም ነው። « እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ ለትውልደ ትውልድ» አቤቱ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንክ የሚለው የዳዊት ሃይለ ቃል የመዝሙሩ መክፈቻ ነው። መዝሙር 89፥1። ከልጅነት ዘመኔ ጀምሮ ሁል ጊዜ የሚደንቀኝ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን የዳዊትን ኃይለ ቃል ለምን የመዝሙር ምስጋናዋ መክፈቻ እንዳደረገችው ነበር።
ሆኖም ግን መዝሙሩን በጥንቃቄ ስመለከት የሚያስተምረውን አስደናቂ ዘላለማዊ እውነት ለመረዳት ቻልኩ።
በዚህ በሃገረ አሜሪካ 2013 ዓ.እ ለመቀበል በዋዜማው ላይ ሳለን፥ በምዕራቡ ዓለም እንደሚኖሩት እንደማናቸውም ሰዎች 2012 ዓእ መለስ ብዬ ለማየት ሞከርኩ። ድካሜንና ብርታቴን፤ ስኬቴና ሽንፈቴንም አሰላሰልኩ፤ በዚህ ሁሉ ግን ወደአእምሮዬ ላይ የመጣው ይህ ከልጅነት ጀምሮ አእምሮዬ ላይ የተቀመጠው የመዝሙረ ዳዊት ኃይለ ቃል ነው። « አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መሠረት ሆንክ፤»