Saturday, December 22, 2012

ዘመነ ስብከት እና መልእክቱ

ከጌታ ልደት በፊት ያሉት ሦስቱ እሑዶች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ግጻዌ ( lectionary) መሠረት ስብከት፥ ብርሃንና ኖላዊ ይባላሉ። በእነዚህ ሳምንታት ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ፡ ኅቡዓት የተሰኘውን የቤተ ክርስቲያን የጸሎትና የዜማ ክፍል ታዜማለች። የክርስቶስ ሰው መሆንና በእርሱም ያገኘነውን ክብር የመስቀሉን ክብር የሚያመልክት ዜማ ነው።

ከዚሁም ጋር በእነዚህ ሳምንታት ከዳዊት መዝሙራት ላይ፥ አቤቱ ከዓርያም እጅህን ስደድልን ( መዝ 143፥ 7) ፥ አቤቱ ብርሃንና ጽድቅህን ላክልን ( መዝ 42፥3) የእስራኤል እረኛ ሆይ አድምጥ፥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ (  መዝ 79፥1) በማለት ከወንጌል ንባብ በፊት በሚዜመው የወንጌል መቅድም (ምስባክ) ላይ እናዜማለን። በወንጌላቱም በነቢያት በሐዋርያት የተሰበከለት ጌታ እንደተገለጠ፥ ይህም በሥጋ የተገለጠው ጌታ የዓለም ብርሃን እንደሆነና ነፍሱን ስለበጎቹ በማኖር በጎቹን ወደሕይወት የሚመራ መልካምና በጎ እረኛ እንደሆነ እናነባለን።

እጅህን ስደድልን . .  ብርሃንን . . . አድምጥ. . . ተገለጥ . . . የሚለው ቃል፥ የቀደሙት ነቢያት  የጌታን በሥጋ መገለጥ በምን ዓይነት ሁኔታ ይጠብቁ እንደነበር የሚያመለክት ነው።

አሁን ጌታ ከተወለደ በኋላ ይህን ዘመነ ስብከት ( Season of Advent) ለምን ሠሩልን የሚል ጥያቄ ላለን ስምዖን ዘዓምድ የጸለየው ጸሎት በቂ መልስ ይሆነናል፤

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ልደትህን በዋሻ ውስጥ ያደረግህ፥ ምስጋናህ በሰማይና በምድር የመላ ሲሆን  ማደሪያ እንደሌለው ደኃ በግርግም ውስጥ የተኛህ፥ ድንቅ የሆነውን ልደትህን እቀበል ዘንድ፥ ሕሊናዬን ዋሻህ አድርገው። ልቡናዬ የመላእክትን መዝሙርና ምስጋና ይማርና ዛሬ መድኃኔ ዓለም ተወልደ፤ ዛሬ በምሕረቱ የሚያሰማራን፥ እንደፈቃዱም የሚመገበን እረኛ ተወለደልን፤ ዛሬ የሕይወት ኅብስት ተዘጋጀልን ተሰጠን ይበል። ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ሕሊናዬን ለምስጋናህ ማደሪያ በረት እንዲሆን አድርገው። ታላቅ የሆነውን ውበትህን ይየው፤ ነፍሴም ሕይወት ሰጪ የሆነውን መዓዛህን ታሽትተው። 

በመሆኑም ይህ ዘመነ ስብከት፥ በሥጋ የተገለጠው አዳኝና መድኃኒት ወደሕይወታችን እጁን እንዲሰድ፥ ብርሃኑን እንዲገልጥልን፥ ጩኸታችንን እንዲያደምጥና በክብር እንዲገለጥ ነው። ከሁሉም በላይ በገናነቱ በጌትነቱና በድንቅ ፍቅሩ በልባችን እንዲወለድ ነው። 

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሕሊናዬን ለምስጋና ማደሪያ በረት አድርገው፤ ታላቅ የሆነውን ውበትህን ይየው። አሜን 

3 comments: