Monday, December 31, 2012

ዘመን ሲለወጥ



እጅግ ደስ ከሚያሰኙኝ የልጅነት ትዝታዎቼ መካከል፥ በዕለተ ሰንበት ከወላጅ አባቴ ጋር በመሆን ወደቤተ ክርስቲያን በመሄድ አብሬያቸው የሰናብቱን መዝሙር መቆም ነው። « እግዚኦ ጸወነ ኮንከነ ለትውልደ ትውልድ» አቤቱ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንክ የሚለው የዳዊት ሃይለ ቃል የመዝሙሩ መክፈቻ ነው። መዝሙር 89፥1። ከልጅነት ዘመኔ ጀምሮ ሁል ጊዜ የሚደንቀኝ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን የዳዊትን ኃይለ ቃል ለምን የመዝሙር ምስጋናዋ መክፈቻ እንዳደረገችው ነበር። 

ሆኖም ግን መዝሙሩን በጥንቃቄ ስመለከት የሚያስተምረውን አስደናቂ ዘላለማዊ እውነት ለመረዳት ቻልኩ። 

በዚህ በሃገረ አሜሪካ 2013 ዓ.እ ለመቀበል በዋዜማው ላይ ሳለን፥ በምዕራቡ ዓለም እንደሚኖሩት እንደማናቸውም ሰዎች 2012 ዓእ መለስ ብዬ ለማየት ሞከርኩ።  ድካሜንና ብርታቴን፤ ስኬቴና ሽንፈቴንም አሰላሰልኩ፤ በዚህ ሁሉ ግን ወደአእምሮዬ ላይ የመጣው ይህ ከልጅነት ጀምሮ አእምሮዬ ላይ የተቀመጠው የመዝሙረ ዳዊት ኃይለ ቃል ነው። « አቤቱ አንተ ለትውልድ ሁሉ መሠረት ሆንክ፤» 

ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት ጊዜ በሁለት ይከፈላል። አንደኛው የጊዜ ክፍልፍሉ፥ አንድ ሁለት ብለን በጊዜ ቅንጣት ፥በሰከንድ፥ በደቂቃ፥ በሰዓት፥ በቀን፥ በወር፥ በወቅት፥ በዓመትና በክፍለ ዘመን የምንቆጥረው ነው። ይህ በግሪኩ ክሮኖስ የምንለው ነው። Chronology, Chronicles  የመጣው ከዚህ ነው። ሌላው ደግሞ በዘመን በጊዜ በሰዓትና በደቂቃ ውስጥ ያለው ክስተት ነው። በግሪኩ ካይሮስ ይሉታል። ካይሮስ ጊዜ ይዞት የሚመጣው ደግም ይሁን ክፉ ነገር ነው። ካይሮስ ካስተዋልነውናን ቆም ብለን ካሰላሰልንበት ብዙ ነገር ያለው ነው። 

ዘማሪው ይህን ኃይለ ቃል ሲዘምር ባሳለፈው ዘመን በከፍታውና በዝቅታው በጊዜ ክስተት ( በካይሮስ) ውስጥ እግዚአብሔር ያልተለየው መሆኑን ነው። የመጀመሪያው እውነት እግዚአብሔር ከዘመናት በፊት የነበረ የዘመን ጌታና ባለቤት መሆኑን ነው የሚናገረው። « ዘእንበለ ይቁም አድባር ወይትፈጠር ዓለመ ወምድረ ወእስከ ለዓለም አንተ ክመ።» ተራሮች ሳይቆሙ፥ ሰማይና ምድር ሳይፈጠር ከጥንት ጀምሮ አንተ ነበርክ» በማለት ይናገራል። 

ጥድፊያ በሞላበት ዓለም ላይ፥ ዛሬ የምናየው ነገ በሚቀየርበት ሕይወት ውስጥ፥ ለዘላለም የጸና የማይለወጥ በዘመናት የሸመገለ አምላክ መኖሩን ማስተዋል እንዴት ደስ ያሰኛል። ልጆች ሳለን አባታችን ወይም እናታችን በቤት መኖራቸው፥ የኑሮአችን ስክነትና መረጋጋት ምልክት ነበር። « አባባ አለ፤ እማማ አለች» እንል ነበር፤ በእፎይታ። አሁን በዚህ አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ለልጆቹ የሚለን ነገር ቢኖር « ዘላለማዊ አባት፥ በዘላለም እውነት ላይ የጸና አባት አለ ነው» ይለናል። « አባ አባ ብለን የምንጮህበትን መንፈስ የሰጠን እርሱ አይደለ?» 

ባለፈው ዓመት ሰዓቱን ከቀናት፥ ቀናቱን ከወራት ስንቆጥር፥ በሕይወት ጉዞአችን ምን አይነት ክስተቶችን (moments)እንዳሳለፍን እያንዳንዳችን እናውቀዋለን። አንድ ጸሐፊ እንዳለ፥ በቀን ውስጥ በትንሹ ከ1440 በላይ ክስተቶች ይኖሩናል ብሎአል። አንዱን ደቂቃ እንደ አንድ ክስተት ወስዶት ነው። እርግጠኛ ነኝ፥ አንዳንድ ጊዜ አንዱ ደቂቃ ራሱ ሺ ክስተት ይዞ ይመጣል። ጥያቄው በዚህ ሁሉ ጊዜ ምን ተማርንበት፤ ታነጽንበት፥ ንስሐ ገባንበት፥ ተገሠጽንበት፥ ጊዜውን ዋጅተን በጥበብ ተመላለስንበት? 

ልዑል እግዚአብሔር « በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ፥ በመዳንም ቀን ረዳሁህ» ይለናል። ጳውሎስ ይህን ሲተረጉም « የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤ የመዳንም ቀን ዛሬ ነው ይላል።» የተወደደው ሰዓት አሁን ነው። 
አሁን ሰከንድ ከሆነ 31,536,000 አሁኖችን አሳልፈናል
አሁን ደቂቃ ከሆነ 525,600 አሁኖችን አሳልፈናል። 
አሁን ሰዓት ከሆነ 8,760 አሁኖችን አሳልፈናል። 
አሁን ቀን ከሆነ 365 አሁኖችን አሳልፈናል። 
አሁን ዓመት ከሆነ 1 አመት በዕድሜያችን ላይ ጨምረናል። 

ሆኖም ሰከንዶቹን ብዙም ሳላላየናቸው ደቂቃዎቹን አላከበርናቸውም። ደቂቃዎቹን ስላላከበርናቸው ሰዓቶቹ ሳናውቃቸው አልፈውናል፤ እንዲህ እያልን ሳናውቀው የአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ ደርሰናል። ያለ ካይሮስ ክሮኖስ ዋጋ የለውም፤ ክሮኖስ ስሌት ብቻ ነው የሚሆነው። አንድ ሁለት ብሎ መቁጠር ብቻ፤ ዋናው የተወደደውን ሰዓት አሁንና ዛሬን ማስተዋል ነው። የተወደደ ሰዓት የተባለው እርሱ ነው። እግዚአብሔር ጸሎታችንን የሚሰማበት፥ ንስሐችንን የሚቀበልበት፤ ክሮኖስን ለማወቅ የቀን መቁጠሪያ ሰሌዳን ማየት ወይም ሰዓትን መመልከት፥ ዓበቅቴውን መጥቅዑን ማውጣት ነው። ካይሮስን ለመመልከት ግን በእያንዳንዱ ደቂቃ « እግዚኦ ፀወነ ኰንከነ» ማለት ነው። አቤቱ አንተ መጠጊያ ሆንከን፤ ለትውልደ ትውልድ፤ በዘመናት ሁሉ፤ በማግኘቴ በማጣቴ በመገፋቴ በመክበሬ፤ በመውደቄ በመነሳቴ፤  የማይለወጠውን የጊዜ ባለቤት በሚለዋወጠው ጊዜ ውስጥ በማየት።  

Happy New Year 

ከሲያትል ወደ ሎስ አንጀለስስ 10 ሺ ጫማ ከፍታ በላይ ላይ ተጻፈ። 

4 comments:

  1. egziabher yebarekeh kesis

    ReplyDelete
  2. Dekike-Abew ke GermanJanuary 1, 2013 at 3:15 PM

    KALE HIWOTIN YASEMALIN KESSIS! YEAGELGILOT ZEMENIHIN YIBARKILIH!

    ReplyDelete
  3. Kesis Melaku kale hiwot yasemalen

    ReplyDelete