ምዕራፍ ፬፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ የእጅህ ሥራ በሙስና ወድቆ ባየህ ጊዜ፥ ልትመልሰውና፥ ዳግመኛ በቸርነትህ ልታድሰው ርኅራኄህን በላዩ አደረግህ። ከትእዛዝህ በመራቁ በሞት ማኅፀን ውስጥ የገባውን ሰውን ታድነው ዘንድ፥ በማኅፀን አደርክ። በርጉም ሰይጣን አሳችነት፥ አዳም በደለ። ትእዛዝህንም ሻረ። አንተ ግን በምሕረትህ አዳንከው፤ በይቅርታህም ድቀት በሌለው መነሣት አነሣኸው።
ምዕራፍ ፭፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፥ ምጽአትህንና በሰው ልጅ ሥጋ ማደርህን ያውጅ ዘንድ ገብርኤልን የላክኸው፥ አንተን ደስ ለሚያሰኝ በጎ ምግባር ሁሉ የተዘጋጀሁ እሆን ዘንድ፥ ከአንተ የሆነውን ኃይልህን በውስጤ አሳድር።
ምዕራፍ ፮፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ወደሚታየው ወደዚህ ዓለም የወርድህ፥ የመንፈሳውያንን አምልኮ እማር ዘንድ፥ በምስጋናቸው አመሰግንህ ዘንድ በቡራኬያቸው እባርክህ ዘንድ፥ ወደ ልቡናዊት ማደሪያህ ከፍ ከፍ አድርገኝ። ይህንን በጸጋ ከአንተ ስጠኝ፤ እንደፈቃድህም መግበኝ፥
ምዕራፍ ፯፡ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ፥ ሥውር ከሆነው እቅፍና ቦታ መጣህ። በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደርክ። ይህችውም መንፈስ ቅዱስ የቀደሳትና መቅደሱ ያደረጋት፥ የሰው ፍጥረት መመኪያ ናት። አሁንም በልቡናዬ ታድር ዘንድ ከልዑላውያን ጋር አመሰግን ዘንድ ከአምልኮአቸው ጋር እተባበር ዘንድ ፥ ልቡናዬን ወደ ሥውሩ ማደሪያህ ከፍ ከፍ አድርገው።
No comments:
Post a Comment