Friday, February 15, 2013

የእስክንድርያ ትምህርት ቤት (ክፍል ሦስት )

የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ፕሮግራም

የትምህርት ቤቱን እንቅስቃሴ በቴዎሎጂ  ብቻ መወሰን ከባድ ስህተት ነው። ትምህርት ቤቱ የዕውቀት መዝገብ ነው።  በመጀመሪያ ትምህርት ቤቱ በጊዜው የነበሩትን የሳይንስ ትምህርቶች በሙሉ የሚያቀርብ ሲሆን፥ ከዚያም ወደሞራልና የሃይማኖት ፍልስፍና ከፍ ይላል። በመጨረሻም በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ላይ ወደተመሠረተው የነገረ መለኮት ትምህርት (ቴዎሎጂ) ይመጣል። መዝገበ ዕውቀታዊ (Encyclopedic) የትምህርት አሰጣጥ መርህ የእስንድርያ ትውፊት ነው። ይኸውም በእስክንድርያ የግሪኮች (አረማውያን) እና የአይሁድ ትምህርት ቤት ውስጥም የሚገኝ ትውፊት ነው።

ታዋቂ ከሆኑት የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህራን መካከል አንዱ የሆነው ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ ነው። እርሱም  1.  ፕሮትሬፕቲከስ ለአሕዛብ ተግሣጽ ( Protrepticus፡ An Exhortation to the Heathen) 2. ፔይዳጎጎስ አስተማሪ Paidagogos (the Educator) 3. ስትሮማታ የተውጣጣ (እስትግቡዕ  Stromata (Miscellanies) የተባሉ መጻሕፍትን ጽፎአል። እነዚህ መጻህፍቱ፥ በእርሱ ጊዜ በእስክንድርያ ትምህርት ቤት የነበረውን ፕሮግራም የሚገልጡ ስለሆኑ በእነዚህ መጻሕፍት ላይ በመመሥረት በዚያን ጊዜ ሦስት ዋና ዋና የትምህርት ክፍሎች እንደነበሩ እናያለን። እነዚህም፡-


1. ደቀ መዛሙርትን ከክርስትና መሠረታዊ ትምህር ጋር የሚያስተዋውቅ ወደ ክርስትና ላልገቡ ሰዎች የሚሰጥ ትምህርት  
2. ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር  
3. ለመንፈሳዊ ሰው የሚገባ መለኮታዊ ዕውቀትን የሚሰጥ ከፍተኛ ትምህርት 

በትምህርት ቤቱ ውስጥ አምልኮ ከትምህርቱ ጋር ጎን ለጎን ይሄድ ነበር። መምህራኑና ተማሪዎች ጸሎትን ጾምን እና የተለያዩ መንፈሳዊ ተጋድሎዎችን ይለማመዱ ነበር። ከመብልና ከመጠጥ ብቻ ሳይሆን ከምድራዊ ሀብትም በመራቅ በመንፈሳዊ ድህነት (በመንኖ ጥሪት) ይኖሩ ነበር።   በንጽሕና እና በቅድስና ሕይወታቸው ምሳሌ ነበሩ። የብቸኝነት (የብህትውና) ሕይወት የሚበረታታና በብዙዎች ተቀባይነት ያገኘ ሕይወት ነበር።   ጂን ዳንኤሉ Jean Daniélou፥ አርጌንስ በተባለው መጽሐፉ ላይ እንዳለው « በዚያን ወቅት ፈላስፋዎች ማለት ጥበብን ተግባራዊ ለማድረግ ጽንሰ ሐሳብን የሚያስተምሩ አልነበሩም፤ ፈላስፋዎች ማለት ስለጊዜዊ ጉዳዮች ማለትም ስለፖለቲካ ወይም ስለምድራው ሙያ መጨነቅን ያቆሙና የነፍስን ጉዳይ ያስቀደሙ ናቸው። የንግግር አዋቂ (rhetorician ) ግብ በዚህዓለም የሚገኘውን ክብር ማግኘት እንደሆነው ሳይሆን  የፈላስፋ ግብ ፍጹማዊ ሕይወት ላይ መድረስ ነው። በዚህም ምክንያት በጥንቱ ዓለም መመለስ ማለት ወደፍልስፍና ( ማለትም ፍጹማዊ ሕይወትን ለመፈለግ) መመለሰ ማለት ነበር።»   

No comments:

Post a Comment