የእስክንድርያ ትምህርት ቤት
በቀሲስ ቴድሮስ ማላቲ
ትርጉም በሊቀ ኅሩያን ቀሲስ መልአኩ ባወቀ ተረፈ
ክፍል አራት
የእስክንድርያ ቴዎሎጂ መለያ ባህርያት
ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ፥ ስለፍልስፍና እና ስለ ዕውቀት (ግኖሲስ) የእስክንድርያ ትምህርት ቤት ያለውን ዕይታ፥ በሌሎች ምዕራፎች ላይ የምንመለስ ሲሆን አሁን ግን የእስክንድርያ ትምህርት ቤትን መለያ ባህርያትን እናያለን።
1.የመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይነት (Deification) ወይም የተሐድሶ ጸጋ (The grace of renewal)
ብዙዎች ምሑራን እንደሚስማሙበት የእስክንድርያ ነገረ መለኮት እምብርት የመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይነት ወይም የተሐድሶ ጸጋ ነው። የመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይነት ማለት በወደቀው የሰው ባህርይ ፈንታ የሰው ባህርይ በአጠቃላይ ታድሶ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ባህርይ ተካፋይ መሆኑ ነው። ወይም ሐዋርያቱ እንደአስተማሩት አማኝ « የመለኮቱ ባህርይ ተካፋይ» መሆኑ(2 ጴጥ 1፥4) ወይም በእግዚአብሔር ምሳሌ አዲሱ ሰው ሲሆን ነው። ( ቆላ 3፥10) ይህ የነገረ መለኮት አስተሳስሰብ እስክንድርያዎችን በነገረ መለኮት ቃላቶችና ብያኔዎች ዙሪያ ከሚደረግ ክርክር በማራቅ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከእግዚአብሔር አብና ከአንድ ልጁም ከወልድ ከኢየሱስ ጋር አንድ በመሆን የመለኮትን ጸጋ ለማግኘት ወይም የወደቀውን ባህርያችንን ካደሰው ከክርስቶስ ጋር አንድ መሆን ላይ እንዲያተኩሩ አስችሎአቸዋል።
ስለዚህ ከሰማይ ወረደ
ስለዚህም የሰውን ባህርይ ገንዘብ አደረገ፤
ስለዚህም የሰውን መከራ ለመታገስ ፈቃደኛ ሆነ
በደካማነታችን መጠን ዝቅ በማለት፤ በኃይሉ መጠን ከፍ አደረገን፤
የእግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ፤ ሰው እንዴት አምላክ እንደሚሆን ትማሩ ዘንድ።
ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ
የእስክንድርያ አባቶች የነገረ መለኮት አስተሳሰባቸው በመላ ያተኮረው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ነው። የእግዚአብሔር ጸጋ፥ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከአብና ከወልድ ጋር ኅብረትን የሚሰጠን ባህያችንን የሚለውጥ የተሐድሶ ጸጋ ይኸውም ከእግዚአብሔር ጋር የሚሆን አንድነትና ኅብረት ነው። በክርስቶስ ኢየሱስ ያገኘነው በመንፈስ ቅዱስ የሆነ የኃጢአት ይቅርታን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን " አዲስ ሕይወት" አግኝተናል። ይህም አዲስ ሕይወት ከኃጢአት ነጻ የሆነ መለኮታዊ ጸጋ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ «አሮጌውን ሰው አስወግዱ» ወይም የተበላሸውን ባህርይ አስወግዱ፥ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ የታደሰውን አዲሱን ተፈጥሮ ወይም በእግዚአብሔር ጽድቅና ቅድስና የተፈጠረውን አዲሱን ሰው " ውስጣዊን ሰው" ልበሱ ይለናል። 2 ቆሮ 5፥21፤ ሮሜ 8፥1) በመለኮታዊ ጸጋው የክርስቶስ አካል አባላት፥ የእግዚአብሔር ልጆች፥ እና የቅድስና ሕይወትን እንድንኖር እንድንኖር ኃይልን የተቀበልን ነን። ምክንያቱም በክርስቶስ ተቀድሰናል፥ ወደ አብም ቀርበናል። አማኝ በሁለንተናው፥ በነፍሱ፥ በአካሉ፥ በስሜቱና በአእምሮው የጽድቅ መሣሪያ ለመሆን ተቀድሶአል። (ሮሜ 6፥13) ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ በአማኙ ሕይወት ውስጥ መለኮታዊ ሥጦታ ሆኖ ይገኛል። ዘላለማዊና ሰማያዊ ክብርን እንደሚገባለት ሁሉ ፥ አሁን ለአማኙ ውስጣዊ ክብር ይሰጠዋል።
ይህ የሰው ተፈጥሮ መታደስ ነው " የመለኮታዊ ክብር ተካፋይነት" የሚባለው። ይህም የተባለው መለኮታዊ ባህርዩን ስለሚያካፍልና ክርስቶስን የእኛ ጽድቅና ቅድስና አድርጎ ስለሚቀበል ነው። ( 2 ጴጥ 1፥4፤ 1 ቆሮ 1፥30) የእስንድርያ ነገረ መለኮት በሚከተሉት ቃላት ተጠቅልሎ ሊገለጥ ይችላል:- " እግዚአብሔር ሰውነትን ወሰደ፤ ሰው ሕይወቱን ይጋራ ዘንድ።" ወይም " እግዚአብሔር ሰው ሆነ፤ ሰዎች አማልክት ይሆኑ ዘንድ"
ጆሴፍ ስቲለር እንደተናገረው ምዕራቡ የክርስትና ክፍልና ምስራቁ ክፍል የክርስቶስን ሥራ የሚገልጡት በተለያየ መንገድ ነው። በምዕራቡ ዓለም የክርስቶስ ሥራ ከኃጢአት በመቤዠት ላይ ያተኮረ ነው። በምሥራቅ ደግሞ የክርቶስ ሥራ ሰውን በማክበር ላይ ያተኮረ ነው። የምዕራቡ ትምህርት የመዋጀት ትምህርት (The doctrine of atonement) ማዕከላዊ ትምህርት ነው፤ በአንጻሩ በምሥራቁ ደግሞ ሱታፌ፥ አብርሆት፥ እና መለወጥ ነው። የምዕራቡ አዳኝ የምስራቁ ፓቶክራቶር (አኃዜ ኩሉ) ነው።
No comments:
Post a Comment