Read in PDF
ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም።
ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋራ በነበረ የአብ አንድ ልጁ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን።
መግቢያ
በነገረ መለኮት ትንታኔው የሚታወቅ አንድ ሊቅ ሲናገር የሃይማኖት ስህተቶች ሁሉ የሚጀምሩት የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ መገለጥ ባለመረዳት ነው ብሎአል። በመሆኑም የጸሎተ ሃይማኖት መሰጠትንም ሆነ ከኒቅያ ጉባኤ በኋላ ያለውን ጊዜ ተከትለው የተደረጉትን ጉባኤያት ብንመለከት በአብዛኛው የሚያጠነጥኑት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የሚሰነዘሩት የስህተት ትምህርቶችን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ልንገልጣቸው ቶማስ አኵናስ የተባለው ሊቅ ይነግረናል።
• ክርስቶስ ሰው ብቻ ነው የሚሉ፤
ለምሳሌ ፎጢኖስ የተባለው « ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም፤ ነገር ግን መልካም ሰው ነው። በመልካም አነዋወሩና ሕይወቱ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማድረጉ በማደጎ (adoption) የእግዚአብሔር ልጅ ተብሎ ተጠርቶአል» በማለት አስተምሮአል። ያ ብቻ አይደለም የክርስቶስ ሕልውና የሚጀምረው ከማርያም ከተወለደ በኋላ ነው በማለት ክርስቶስ በጊዜ የተወሰነ እንደሆነ አስተምሮአል። የእግዚአብሔር ቃል ግን እነዚህ አስተሳሰቦች ሐሰት እንደሆኑ በግልጥ ይመሰክራሉ። ዮሐንስ በወንጌሉ « እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለው አንድ ልጁ እርሱ ተረከው» በማለት ወልድ በቅድምና ከአብ ጋር እንደነበር ይናገራል። ዮሐንስ 1፥18፤ ኢየሱስም ራሱ « አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ» ብሎ ሲናገር ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከመወለዱ በፊት ከአብርሃም በፊት መኖሩን ነግሮናል። ዮሐንስ 8፥58።
• ክርስቶስ ራሱ አብ ነው የሚሉ፤
በዚህ ስህተቱ የታወቀው ሰባልዮስ የተባለው ሰው ነው። ሰባልዮስ ጌታ ቅድመ ዓለም መኖሩን ያምንና ነገር ግን በሥጋ የተገለጠው ቅድመ ዓለም የነበረው አብ ነው ብሎ ያስተምር ነበር። በእርሱ ትምህርት አብና ወልድ ሁለት አካላት ሳይሆኑ አንዱ አብ ነው በተለያየ መንገድ የተገለጠው። አሁንም የሰባልዮስን ስሕተት የእግዚእብሔር ቃል በግልጥ ይቃወመዋል። ጌታ ራሱ « የላከኝ አብ ከእኔ ጋር ነው እንጂ ብቻዬን አይደለሁም» በማለት ከአባቱ እንደተላከ» በዮሐንስ 8፥16 ላይ ገልጦአል።
• ልዩ ፍጡር ነው የሚሉ፤
አርዮስ የተባለው የስሕተት አስተማሪ ስለጌታ ያስተማረው ትምህርት ከቅዱሳት ጋር የሚቃረን ነበር፤ አንደኛ ክርስቶስ ፍጡር ነው። ሁለተኛ፥ ከዘለዓለም ያልነበረና ከሌሎች ፍጡራን ልዩ አድርጎ እግዚአብሔር የፈጠረው ነው ። ሦስተኛ፥ በባሕርዩ ከአብ ጋር አንድ ስላይደለ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም እውነተኛ አምላክ አይደለም በማለት ያስተምር ነበር። አሁንም የአርዮስን ትምህርት መጽሐፍ ቅዱስ ሲሽርበት ጌታ « እኔና አብ አንድ ነን» በማለት በባሕርይ ከአባቱ ጋር አንድ መሆኑ ሲገልጥ እናያለን።
እነዚህ ከላይ ያያናቸው በየዘመኑ ከተነሡት ለናሙና ያነሣናቸው ስህተቶች ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በክርስቶስ ላይ ለሚሰነዘሩት ስህተቶች መሠረቶች ናቸው። « የኑፋቄ አዲስ የለውም» የሚባለው ለዚህ ነው። ሆኖም ቶማስ አኵኖስ ይህ ሁሉ በየጊዜው የሚነሣው ስህተት ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ መክፈቻ ላይ ያስቀመጣቸው ዐረፍተ ነገሮች « በመጀመሪያ ቃል ነበር» የፎጢኖስን « ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ» የሰባልዮስን፥ « ቃልም እግዚአብሔር ነበረ» የአርዮስን ስህተት ይደመስሰዋል ብሎአል ።
ኢየሱስ ማንነው?
በጊዜው በሥጋ ያዩት የሃይማኖት መሪዎች፥ የሕዝብ አስተዳዳሪዎች፥ ደቀ መዛሙርቱ እና ሌላውም ሕዝብ በአንድነት የጠየቁትን ጥያቄ እርሱ ማንነው? የሚል ነው። እኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው በማለትና በመጠየቅ ስለ አዳኛችን ስለመድኃኒታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በጥልቀት እናጠናለን።
ሽባውን ሰው « ኃጢአትህ ተሰረየችልህ» ሲለው ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ያሉት « ይህ የሚሳደብ ማን ነው? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ማን ይችላል? ብለው ያስቡ ጀመር።» ሉቃስ 5፥21። እንደገና ኃጢአተኛዋን ሴት « ኃጢአትሽ ተሰርዮልሻል» ሲላት በማዕድ ከርሱ ጋር ተቀምጠው የነበሩት « ኃጢአትን እንኳ የሚያስተሰርይ ይህ ማን ነው?» ብለው ነበር። ሉቃስ 7፥48-49። ዮሐንስን ያስገደለው ሄሮድስም « ዮሐንስንስ እኔ ራሱን አስቈረጥሁት፤ ይህ እንዲህ ያለ ነገር የምሰማበት ማን ነው? » በማለት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለማየት አጥብቆ ይሻ እንደነበረ ሉቃስ ይነግረናል? ሉቃስ 9፥9። ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባና ከተማዋ ስትናወጥ ሕዝቡ « ይህ ማነው?» በማለት ነው የጠየቁት። ደቀ መዛሙርቱም በብዙ ቦታ ስለጌታ የበለጠ ለማወቅ ፈልገው በፍርሃት ዝም እንዳሉ እናያለን? ሉቃስ 9፥45።
በእነዚህ ሁሉ ሰዎች እና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከሁን በተነሳውም ትውልድ ይህ ማነው የተባለውን፥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በኒቅያ የተሰበሰቡ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች የገለጡበትን መንገድ ለመረዳት በወንጌል ላይ ጌታ ስለራሱ የተናገረውን መረዳት ይገባል።