Read in PDF
ተሰብአ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል።
ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ፈጽሞ ሰው ሆነ
መግቢያ
ባለፈው ክፍላችን ስለ እግዚአብሔር ወልድ ስለ ሐልዎቱ ቅድመ ዓለም ስለነበረው አነዋወሩ አባቶች ያስቀመጡትን ሀረግ አይተናል። በዚህ ክፍላችን ደግሞ በባሕርያችን መመኪያ በቅድስት ድንግል ማርያም የተከናወነወነውን አስደናቂ ሥራ እናያለን።
ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ስናነሣ፥ ኦርቶዶክሳውያን መምህራን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር ለማሰላሰል ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ማንነት ለመጻፍ፥ ለማስተማር መነሻ ያደረጉት ምንድነው የሚል ነው? ለማንኛውም መንፈሳዊ እውነት መነሻችን የእግዚአብሔር ቃል እንደመሆኑ መጠን ኦርቶዶክሳውያን መምህራን መነሻ ያደረጉት መጻሕፍት አምላካውያት የአምላክ መጻሕፍት ብለው የሚጠሩዋቸውን ቅዱሳት መጻሕፍትን መነሻ አድርገው ነው። ይህ ወደሚቀጥለው ጥያቄ ይመራናል። ቅዱሳት መጻሕፍትን የተገነዘቡት ወይም ያነበቡት እንዴት ነው? መረጃ እንዳለበት መጽሐፍ በማየት ኢንፎርሜሽን ነው የሰበሰቡት ወይስ የእግዚአብሔር ቃል የአምላክን ልጅ በሥጋ መገለጥ የሚያውጅ መጽሐፍ መሆኑን በመመልከት የመሲሑን መምጣት እና ለመምጣቱ ምን ዓይነት ዝግጅት እንደነበረው በመመርመር ነው? የዚህ ጥያቄ አመላለሳችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የሚኖረንን አመለካከት በብዙ መንገድ የሚወስነው ይሆናል?
መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መረጃ መጽሐፍ ብቻ የምንመለከት ከሆነ በዚህ በአገረ አሜሪካ የታወቀ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንዳለው « ስለዚህች ማርያም መጽሐፍ ቅዱስ ብዙም አይናገርም» በማለት ታላቁን የእግዚአብሔር የማዳን ታሪክ እንደቀልድ እናልፈዋለን። ነገር ግን እንደኦርቶዶክሳውያን አባቶች መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ስለመገለጡ የሚናገር መጽሐፍ ከሆነ ስለቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር በቃሉ የሚናገረውን ከዘፍጥረት መጽሐፍ ከመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ጀምሮ እስከ ራዕየ ዮሐንስ እናያለን። በመረጃነት የተጻፈውን ከሆነ የምንፈልገው 90% የሆነውን የምናገኘው ከሉቃስ ወንጌል ነው። ሆኖም ግን መነሻችን እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ መገለጡ ከሆነ ግን ከአዳም እንጀምራለን። ለዚህም ነው አባቶች በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ታሪክ ውስጥ ክርስቶስን በምሳሌ እንዳገኙት ሁሉ እርሱ የተገለጠባትን ከእርሷ የተወለደባትን ቅድስት ድንግል ማርያምንም በምሳሌ ያገኙት። በዚህ ተመስርተው አባቶች ቅድስት ድንግል ማርያምን ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳንና በእነርሱ ሕይወት ካደረገው ድንቅ ነገር ጋር አስተያይተው ተናግረዋል። ዳግማዊት ሔዋን ብለዋታል። (ዘፍጥረት 3) የያዕቆብ መሰላል ( ዘፍጥረት 28፥12 ብለዋታል፤ የሙሴ ጽላት ብለዋታል። የአሮን በትር ብለዋታል። ። . . .
ስለ ክብረ ቅድስት ድንግል ማርያም የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የነበሩት ፖፕ ሸኑዳ የጻፉትን መመልከቱ ጠቃሚ ስለሆነ በከፊል በዚህ ክፍል ላይ በከፊል ተርጉመን አቅርበነዋል።
« ስለ ድንግል ማርያም ክብር፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገበውን የድንግልን ቃል መጥቀስ ብቻ በቂ ነው፦« ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል።» ሉቃስ 1፥48። « ትውልድ ሁሉ» የሚለው ሐረግ ድንግል ማርያምን ማክበር ለሁሉም የተሰጠ ዶግማ መሆኑና፥ በክርስቶስ ሰው መሆን ተጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ የሚቀጥል መሆኑን የሚያመለክት ነው። ለድንግል ማርያም የተሰጡ ክብሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግበዋል። ለምሳሌ ከቅድስት ማርያም እናት ጋር በዕድሜ እኩያ የሆነችው ኤልሳቤጥ « የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽን ድምፅ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና።» ብላለች። ሉቃስ 1፥43-44) በዚህ ቦታ ላይ ስለ ድንግል ክብር ሊያስደንቀን የሚገባው ነገር ቢኖር የእርሷን ሰላምታ ኤልሳቤጥ ስትሰማ « በመንፈስ ቅዱስ መሞላቷ ነው። (ሉቃስ 1፥41። የድንግልን ድምጽ መስማቷ ብቻ ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ እንድትሞላ አድርጓታል።
ድንግል ክብርን የተቀበለችው ከሰው ዘር ብቻ አይደለም። ከመላእክትም ተቀብላለች። ይህም ከመልአኩ ከገብርኤል ሰላምታ ግልጥ ነው። « ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ። ጌታ ካንቺ ጋር ነው። አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ» ነበር ያላት። ሉቃስ 1፥28። « አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ » የሚለው ቃል ኤልሳቤጥ ለድንግል ማርያም በሰጠችው ሰላምታ ተደግሞአል። ሊቀ መላእክት ገብርኤል ድንግል ማርያምን ሲያናግር የተጠቀመው ንግግር ካህኑ ዘካርያስን ካናገረበት ንግግር ይልቅ ታላቅ ክብር ያለው ንግግር ነበር። ሉቃስ 1፥13።. . .
ቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ሁሉ ምኞት ናት። « የእባቡን ራስ የቀጠቀጠው» ከእርሷ የተገኘው ነው። በዚህም እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን የገባው ተስፋ ተፈጽሞአል። ዘፍጥረት 3፥15።
ድንግል የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት እንደመሆኗ ለክርስቶስ የተሰጡት ማዕረጋት ሁሉ ለእርሷ እናትነትም ይሰጣሉ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ብርሃን ነው። (ዮሐንስ 1፥9) እርሱ ራሱ « እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» ብሎአል። ዮሐንስ 8፥12። ስለሆነም እናቱ ድንግልም የብርሃን እናት ወይም የእውነተኛው ብርሃን እናት ናት። ክርስቶስ ቅዱሱ እንደሆነ ሁሉ (ሉቃስ 1፥35) ድንግልም የቅዱሱ እናት ናት። ለእረኞች « ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና» ተብሎ እንደተነገረ (ሉቃስ 2፥11)እንዲሁ « ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና» ( ማቴዎስ 1፥21) ስሙ ኢየሱስ ይኸውም አዳኝ እንደተባለ ሁሉ ድንግልም የመድኃኒታችን እናት ናት። ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደመሆኑ (ዮሐንስ 1፥1፤ ሮሜ 9፥5) ዮሐንስ 20፥28) ድንግልም የእግዚአብሔር እናት ናት። ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ፥ በኤልሳቤጥ ቃል መሠረት ድንግል ማርያም « የጌታዬ እናት ናት» ተብላ ስለተጠራች (ሉቃስ 1፥43) ድንግል የጌታ እናት ናንት። በተመሳሳይ መንገድ እርሷ የአማኑኤል እናት ናት። ማቴዎስ 1፥24። የሥግው ቃል እናት ናት። ዮሐንስ 1፥14።
ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቶስ እናት ከሆነች ያለምንም ጥያቄ የክርስቲያኖች ሁሉ መንፈሳዊ እናት ናት። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ይወደው ለነበረው ሐዋርያ ለቅዱስ ዮሐንስ « እነሆ እናት» ብሎ የተናገረው በቂ ነው። (ዮሐንስ19፥27 ለእኛ « ልጆቼ » በማለት ለጻፈልን ለቅዱስ ዮሐንስ እናት ከሆነች (2 ዮሐንስ 1፥1) ለእኛም ለሁላችን እናት ናት። . . .
ድንግልን የሚያከብር ክርስቶስን ራሱን ያከብራል። እናትን ማክብር ተስፋ ያለው የመጀመሪያ ትእዛዝ ከሆነ (ኤፌሶን 6፥1፤ ዘፀዓት 20፥12) የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን እናትና የሐዋርያትን እናት ድንግል ማክበር አይገባንምን? መልአኩ « መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ የመጣል፤ የልዑል ኃይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል » ብሎአት ነበር። (ሉቃስ 1፥35) በኤልሳቤጥ የተመሰገነች እርሷ ነች። ኤልሳቤጥ « ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት» ነበር ያለቻት። ሉቃስ 1፥45።
« ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ» የሚለው ቃል በቅዱስ ገብርኤል እና በቅድስት ኤልሳቤጥ ሲነገር፥ ድንግል በመላው ዓለም ከሚገኙት ሴቶች መካከል የተባረከች ሆና መገኘቷን የሚያመለክት ነው። ምክንያቱም በአካላዊ ቃል ሰው መሆን እርሷ የተቀበለችውን መለኮታዊ ክብር የተቀበሉ ሴቶች ስለሌሉ ነው። እግዚአብሔር ድንግል እመቤታችንን የመረጠው እርሷ ያላትን የቅድስና ባሕርይ ያሟሉ ሌሎች ሴቶች ስለሌሉ ነው። ይህም የእርሷን ከፍታ የሚያመለክት ነው። . . .
እግዚአብሔር በእርሷ ውስጥ በማደሩ ቤተ ክርስቲያን እርሷን ዳግማዊት ሰማይ፥ የመገናኛ ድንኳን፥ የሙሴ ድንኳን ብላ ትጠራለች።
ቤተ ክርስቲያን ድንግልን የእግዚአብሔር ከተማ ወይም ጽዮን ብላ ትጠራታለች፤ ምክንያቱም በመዝሙረ ዳዊት « እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፤ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፤ እንዲህ ብሎ፦ ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ና መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።» መዝሙር 131፥13
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ የወረደ ሕብስት እንደሆነ በመናገር በመና ራሱን በመመሰሉ፥ ( ዮሐንስ 6፥58) ቤተ ክርስቲያን ድንግልን የመና ሙዳይ ትላታለች።
በድንግልና አምላክን ስለመውለዷም ቤተ ክርስቲያን አሁንም ድንግልን የአሮን በትር ትላታለች። ( ዘኍልቍ 17፥8-11።
የምስክሩ ታቦትም የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። ምክንያቱም ታቦቱ በውጭም በውስጥም በወርቅ የተለበጠ ነው። ይህም የእርሷን ንጽሕና ክብር የሚያመለክት ነው። ሁለተኛ ታቦቱ ከማይነቅዝ እንጨት የተሠራ ነው። ይህም ቅድስናዋን የሚያመለክት ነው። ሦስተኛው ታቦቱ መናውን የያዘ ነው። ይህም መና ከሰማይ የወረደውን የሕይወት ሕብስት ክርስቶስን የሚያመለክት ነው። በመጨረሻም ታቦቱ የእግዚአብሔር ቃል ክርስቶስን የሚያመለክቱትን ሁለቱን የሕግ ጽላቶች የያዘ ነው። ዮሐንስ 1፥1።
ያዕቆብ በሕልሙ ያየው ከምድር እስከሰማይ የደረሰው መሰላል የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። ሰማይና ምድር በክርስቶስ ሰው መሆን ተጋጥሞአል። እርሷ ሰማይ ያደረባት ምድር ሆናለች። እርሷ በምድር ሆና ሰማይን በውስጧ ተሸክማለችና፤ (ዘፍጥረት 28፥12።)
ሙሴ የተመለከተው እሳቱ ያላቃጠለው ሐመልማል የድንግል ማርያም ምሳሌ ነው። መንፈስ ቅዱስ በመለኮታዊ እሳትነቱ በእርሷ ላይ ሲመጣ አላቃጠላትምና።
የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የመለኮትና የሰውነት ተዋህዶ ፍሕሙንና እሳቱን እንደሚመስል ሁሉ ቅድስት ድንግል ማርያምም ያን ተዋህዶ የተሸከመች እንደመሆኑዋ፥ በማእጠንት ትመሰላለች። በመሆኑም የአሮን ማዕጠንት ወይም ክብሩዋን ለማጉላት የወርቅ ማዕጠንት ተብላ ትጠራለች።. . .