( የዛሬውን ምዕራፍ ምንም እንኳ በአንድ ክፍለ ትምህርት የዘረዘርነው ቢሆንም ካለብን የጊዜ ገደብ የተነሣ መሆኑን እየገለጥን ወደፊት እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ በስፋት እናየዋለን። )
ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እንሰግድለት እናመሰግነው ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋራ በነቢያት የተናገረ፤
ሐዋርያት በሰበሰቡአት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን፤ ለዘለዓለሙ። አሜን።
ሀ. በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን።
የአባቶቻችን አንቀጸ ሃይማኖት ስለመንፈስ ቅዱስ የሚከተሉትን እውነቶች ይነግረናል።
1. ቅዱስ መንፈስ ነው።
ብዙዎች ቅዱሳን ያይደሉ መናፍስት አሉ። ለምሳሌ በጌታ ላይ አምፀው የወደቁት መላእክት ርኩሳን መናፍስት ተብለዋል። የሥላሴ ሦስተኛው አካል ግን ቅዱስ መንፈስ ነው። ማለትም ልዩ ክቡር ንጹህ የሆነ መንፈስ ነው። የእግዚአብሔር የሆነውን የሚቀድስ የሚያነጻ መንፈስ ነው። ሐዋርያው እንደተናገረው «ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።» 1 ቆሮንቶስ 6፥11።
2. ጌታ ነው።
ከዚህ በፊት « ጌታ » ስለሚለው ቃል እንደተመለከትነው፥ ለእግዚአብሔር ብቻ ሊቀጸል የሚችል የእግዚአብሔርን ማንነት የሚገልጥ ስም ነው። ጌታ የሚለው ቃል ሉዓላዊነቱን፥ ከፍታውን የሚያመለክት ነው። መንፈስ ቅዱስ ሉዓላዊ አምላክ ነው። ከፍ ያለ እና በገናንነቱ ያለ አምላክ ነው።
• መንፈስ ቅዱስ ዘላለማዊ ነው (ዕብራውያን 9፥14)
• ሁሉን የሚያውቅ ነው። ( ኢሳይያስ 40፥13፤ 1 ቆሮንቶስ 2፥10_12)
• ሁሉን የመላ ነው። (መዝሙር 138፥7_10
• ሁሉን ቻይ ነው። (ኢዮብ 33፥4)
3. ሕይወት ሰጪ ነው
መንፈስ ቅዱስ ባለበት ቦታ ሁሉ ሕይወት አለ። መንፈስ ቅዱስ በክበበ ሥላሴ ውስጥ ማለትም ከአብና ከወልድ ጋር ባለው አነዋወሩ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው። በምእመናንም ሕይወት መንፈስ ቅዱስ የሕይወት መንፈስ ነው። በኃጢአት የሞተው ሕይወታችን ተነሥቶ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ በስፋት ባስተማረበት በሮሜ 8 ላይ እንዳስተማረን ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት የምናገኘው፥ የእግዚአብሔር ልጆች የምንባለው፥ አባ አባት ብለን ወደ አምላካችን እንድንጮህ ያስቻለን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ነግሮናል።