Tuesday, August 6, 2013

ጸሎተ ሃይማኖት (አሥራ ሁለተኛ ክፍል)

( የዛሬውን ምዕራፍ ምንም እንኳ በአንድ ክፍለ ትምህርት የዘረዘርነው ቢሆንም ካለብን የጊዜ ገደብ የተነሣ መሆኑን እየገለጥን ወደፊት እግዚአብሔር በፈቀደ ጊዜ በስፋት እናየዋለን። ) 

ጌታ ማኅየዊ በሚሆን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እንሰግድለት እናመሰግነው ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋራ በነቢያት የተናገረ፤ 
ሐዋርያት በሰበሰቡአት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን፤ ለዘለዓለሙ። አሜን።

ሀ. በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን። 
የአባቶቻችን አንቀጸ ሃይማኖት ስለመንፈስ ቅዱስ የሚከተሉትን እውነቶች ይነግረናል። 
1. ቅዱስ መንፈስ ነው። 
ብዙዎች ቅዱሳን ያይደሉ መናፍስት አሉ። ለምሳሌ በጌታ ላይ አምፀው የወደቁት መላእክት ርኩሳን መናፍስት ተብለዋል። የሥላሴ ሦስተኛው አካል ግን ቅዱስ መንፈስ ነው። ማለትም ልዩ ክቡር ንጹህ የሆነ መንፈስ ነው። የእግዚአብሔር የሆነውን የሚቀድስ የሚያነጻ መንፈስ ነው። ሐዋርያው እንደተናገረው «ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፥ ተቀድሳችኋል፥ ጸድቃችኋል።» 1 ቆሮንቶስ 6፥11። 

2. ጌታ ነው። 

ከዚህ በፊት « ጌታ » ስለሚለው ቃል እንደተመለከትነው፥ ለእግዚአብሔር ብቻ ሊቀጸል የሚችል የእግዚአብሔርን ማንነት የሚገልጥ ስም ነው። ጌታ የሚለው ቃል ሉዓላዊነቱን፥ ከፍታውን የሚያመለክት ነው። መንፈስ ቅዱስ ሉዓላዊ አምላክ ነው። ከፍ ያለ እና በገናንነቱ ያለ አምላክ ነው። 
• መንፈስ ቅዱስ ዘላለማዊ ነው (ዕብራውያን 9፥14) 
• ሁሉን የሚያውቅ ነው። ( ኢሳይያስ 40፥13፤ 1 ቆሮንቶስ 2፥10_12) 
• ሁሉን የመላ ነው።  (መዝሙር 138፥7_10
• ሁሉን ቻይ ነው። (ኢዮብ 33፥4) 

3. ሕይወት ሰጪ ነው
መንፈስ ቅዱስ ባለበት ቦታ ሁሉ ሕይወት አለ። መንፈስ  ቅዱስ በክበበ ሥላሴ ውስጥ ማለትም ከአብና ከወልድ ጋር ባለው አነዋወሩ ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው። በምእመናንም ሕይወት መንፈስ ቅዱስ የሕይወት መንፈስ ነው። በኃጢአት የሞተው ሕይወታችን ተነሥቶ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግን የሚያደርገው መንፈስ ቅዱስ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ በስፋት ባስተማረበት በሮሜ 8 ላይ እንዳስተማረን ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት የምናገኘው፥ የእግዚአብሔር ልጆች የምንባለው፥ አባ አባት ብለን ወደ አምላካችን እንድንጮህ ያስቻለን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ነግሮናል። 


4. ከአብ የሠረጸ ነው። 
መንፈስ ቅዱስ ከአብ ዘንድ ከዘላለም የሠረጸ( የወጣ) ነው። ጌታ ኢየሱስ ስለሚመጣው አጽናኝ ሲናገር « ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤»  በማለት ተናግሮአል። (ዮሐንስ 15፥26።) በመሆኑም የጌታን ቃል ተከትለን ከአብ የሚወጣ ወይም የወጣ ብለን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን እናከብረዋለን። ሐዋርያው ጴጥሮስም በበዓለ መንፈስ ቅዱስ ወይም በበዓለ ሃምሳ ለተሰበሰቡትና ስብከቱን ለሚሰሙት ሲናገር እንዲህ ብሎአል። «ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን የተስፋ ቃል ከአብ ተቀብሎ ይህን እናንተ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው።» ሐዋ ሥራ 2፥ 33። 

5. ከአብና ከወልድ  ጋር የሚመለክ ነው።   

መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር የሚመሰገንና የሚሰገድለት ነው። ይህንንም የምናደርገው ጌታ እንዳስተማረንና ሐዋርያትም እንደጻፉልን ነው። ጌታ ጥምቀታችን ወይም የጥምቀት ሥርዓታችን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲሆን ነግሮናል። (ማቴዎስ 28፥20) ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የአዲስ ኪዳን ቡራኬ ምን እንደሚመስል ሲያስተምረን «
የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።» 2 ቆሮንቶስ 13፥14።

6. በነቢያት የተናገረ ነው።
የቅዱስ መጽሐፍ ደራሲ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው የምንለው ያለምክንያት አይደለም። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር «

የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።» 2 ጢሞቴዎስ 3፥16። ስለሆነም ቅዱሳት መጻሕፍት የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው። « ይህን በመጀመሪያ እወቁ፤ በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ሁሉ ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ።» 2 ጴጥሮስ 1፥20_21።

ለ. በቤተ ክርስቲያን እናምናለን።
ስለ መንፈስ ቅዱስ ከተናገርን በኋላ ስለቤተ ክርስቲያን የምናነሣው ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ነው። « በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።» ሐዋ ሥራ 20፥28። በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ቤተ ክርስቲያን የሚከተሉት ምልክቶች ይኖሩአታል።

1. ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት።
ክርስቶስ የመሠረታት ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት። (ዮሐንስ 10፥16፤ሮሜ 12፥4፤) ይህ የቤተ ክርስቲያን አንድነት የተገኘው ከሥላሴ አንድነት ነው። (ዮሐንስ 17፥11)አንድ አባት አንድ ጌታ፥ አንድ መንፈስ፥ አንዲት ጥምቀት፥ አንድ እምነት ነው ያለን። (ኤፌሶን 4፥1_15። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደመሆኑ በእርሱ ራስነት ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት። ይህን የክርስቶስ አካል በመንፈስ አንድነት ለመጠበቅ መትጋት የምእመናን ሁሉ ተግባር መሆን አለበት።

2. ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት።
የቤተ ክርስቲያን ቅድስና በራስዋ የተገኘ አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ቅድስናዋና ያገኘችው በእግዚአብሔር ቅድስና ተካፋይ በመሆን ነው። ይህም ሊሆን የቻለው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ በደሙ ስለቀደሳት ነው። ኤፌሶን 5፥25። እኛ ተቀድሰን የተፈጸምን ሳንሆን በሂደት ላይ ያለን ነን። በአንድ በኩል ከክርስቶስ ደም የተነሣ ቅድስናን አግኝተናል። በሌላ በኩል ደግሞ የእግዚአብሔር ቤትና ቅዱሳን ካህናት ለመሆን የምንሠራ ነን። እየተሠራንም እንገኛለን። 1 ጴጥሮስ 2፥9።

3.።ቤተ ክርስቲያን በሁሉ ያለች (ካቶሊኮስ) ናት።
ቤተ ክርስቲያን በጊዜ በቦታ የምትወሰን አይደለችም። ራሷ ክርስቶስ በሁሉ ያለ እንደመሆኑ ቤተ ክርስቲያንም እንዲሁ ናት። ባህል፥ ቋንቋ፥ ብሔር፥ መደብ፥ ፖለቲካና የኢኮኖሚ መዋቅር ቤተ ክርስቲያንን አይገድባትም።  ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ የምታምነው አንዱን እውነት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ እንደመሰከረው። 1 ዮሐንስ1፥1። በሁሉ ቦታ እንዳለችና መኖር እንዳለባት የምታምን ስለሆነች ቤተ ክርስቲያን መልካሙን ዜና (ወንጌልን) ለሰዎች ሁሉ ለማዳረስ ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ትወጣለች።

4.።ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት።
ሐዋርያ ማለት የተላከ ማለት ነው።  ጌታ ለሐዋርያቱ ሲናገር « አብ እንደላከኝ እኔ እልካችኋለሁ።» ዮሐንስ 20፥21። ጌታ ራሱ የእምነታችህን ሐዋርያ ነው። ገላትያ 4፥4፤ ዕብራውያን 4፥4። ከአባቱ የተላከልን። እርሱ ከአባቱ እንደተላከ እርሱ ደግሞ የእርሱ የሆኑትን ወደ አለም ልኮአቸዋል። የእግዚአብሔርን ፍቅር ይሰብኩ ዘንድ። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ተልዕኮ ውስጥ ነው የምትኖረው። ሐዋርያዊት ያሰኛትም ይህ ተልዕኮዋ ነው። ይህ ተልዕኮ በክርስቶስ ትንሳኤ ተጀምሮ በክርስቶስ ዳግም ምጽዓት የሚደመደም ነው። ማቴዎስ 28፥19። 



ሐ. በአንዲት ጥምቀት እናምናለን። 
በመካከለኛው ምሥራቅ ለጉብኝት በሄድኩበት ወቅት ከተነገረኝ አስደናቂ ታሪኮች መካከል እስከ አሁን ከአእምሮዬ የማይጠፋው ስለጥምቀት የተነገረኝ ነው። በዚያ አካባቢ በጥምቀት እምነትን መግለጥ የመጨረሻው የእምነት እርምጃ ነው። ይህ ብዙ ጊዜ የሞት ቅጣትን የሚያመጣ ስለሆነ በብዙ ጥንቃቄ ወደ ውሳኔ የሚደርሱበት ነው። አንድ ሰው እስከሚጠመቅ ድረስ የሌላ እምነት ተከታዮች የሆኑት ቤተሰቦቹ ይታገሱታል፤ ወደ ቀደመ እምነቱ ለመመለስ ይጥራሉ። ከተጠመቀ በኋላ ግን የሚያዘጋጁለት ሞት ነው። ይህ ዓይነቱን ታሪክ ሲነገረኝ የቀደመችውን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ነው ያስታወሰኝ። ጥምቀት ምንድነው? 
1. ጥምቀት ልጅነትን የምናገኝበት መንገድ ነው። 
ጌታ በመንፈቀ ሌሊት ለኒቆዲሞስ የነገረው ነገር ቢኖር ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት እንደማይችል ነው። « ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።» ዮሐንስ 3፥5። 
2. ጥምቀት መንጻትን የምናገኝበት ነው። 
ወደ ጥምቀት የሚወስደው የልብ ዝግጅት ንስሐን የሚጠይቅ ነው። በነቢዩ በሕዝቅኤል እንደተነገረው ከኃጢአት መንጻትን እናገኛለን። « ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።» ሕዝቅኤል 36፥25። 
3. ጥምቀት በንስሓ የሚሆን መታደስን የምናገኝበት ነው። 
በቲቶ ላይ እንደተጠቀሰው ጥምቀታችን አዲስ ሕይወት ለማግኘት ነው። «እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤» ቲቶ 3፥5። 

4. ጥምቀት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር የምንተባበርበት ነው። 
« ወይስ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን?እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን።ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤  ሮሜ 6፥4_5። 

መ. በሚመጣውም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን።

ይህ ያለንበት ሕይወት በእንፍዋሎት ወይም በጤዛ ተመስሎአል። ( ያዕቆብ 4፥14) ዘመናችንም እንደጥላ እንደሆነ ተነግሮናል። 1ዜና 29፥15። ቅዱስ ጴጥሮስም « ሥጋ ሁሉ እንደ ሣር ክብሩም ሁሉ እንደ ሣር አበባ ነውና፤ ሣሩ ይጠወልጋል አበባውም ይረግፋል፤» 1 ጴጥሮስ 1፥24። ሆኖም ግን በዚህ ዓለም ጊዜያዊነት ውስጥ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነትና በእርሱም የተሰጠንን የዘላም ሕይወት እንመለከታለን። ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ከማይጠፋው ዘር ተወልዳችኋል ያለን። 1 ጴጥሮስ1፥23። በመሆኑም ጸሎተ ሃይማኖታችንን የምንደመድመው በዚህ ታላቅ ተስፋ ነው። በሚመጣው ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን። ዛሬ ምድራዊው ሕይወት ከግራ ወደ ቀኝ የሚወዘውዘን በሚመጣው ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን። ዛሬ በምድራዊው ሕይወት በሕመም የምንሰቃይ በሚመጣው ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን። ዛሬ የምንወዳቸው ዘመዶቻችን ወገኖቻችን የተለዩን በሚመጣው ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን። ተስፋችን በሚያልፈውና ለእግዚአብሔር ፍርድ በተሰጠው በዚህ ዓለም ሳይሆን ዓይን ያላየው ጆሮ ያልሰማው በሰው ልቡና ያልታሰበ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጀው የሚመጣው ሕይወት ነው። በዚህ ሕይወት ተስፋ እናድርግ፥ በዚህ ሕይወት በእምነት እንቁም በዚህ ሕይወት  በፍቅር እንመላለስ። የሚመጣው ሕይወት ያው ራሱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በእርሱ መምጣት ሕይወታችንና ክብራችን ይገለጣል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል። በሊቃነ  መላእክት ታጅቦ ልጆቹን አስከትሎ ይመጣል። አሜን ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና። ማራናታ። 







No comments:

Post a Comment