Wednesday, November 13, 2013

ኢትዮጵያዊነት በአደባባይ ሲወድቅ


የፋሽሽት ጣልያንን ወረራ ጊዜና እርሱን ተከትሎ የነበረውን ሰቆቃ ያስተዋሉ ሰዎች፥ ሁሉ አልፎ ነጻነት ካገኙ በኋላ፥ አንዳንድ ጊዜ ነጻነታቸው ሲገፈፍ እና መብታቸው ሲታፈን “ በሕግ አምላክ ወድቆ በተነሣው ባንዲራ!” ይሉ ነበር። ዛሬ በአረብ አገር ላይ ወድቆ እያየነው ያለነው  ባንዲራው ወይም ሕጉ ሳይሆን ኢትዮጵያውነት ራሱ ነው። 
ዛሬ በአረብ አገሮች እንደ አበዱ ውሾች እየታደኑ የሚደበደቡት የሚታሠሩት ኢትዮጵያውያን የሚጮኽላቸው ለዜጎቹ የሚቆምላቸው አካል እንደማይኖር ስለታወቀ ነው። በእኛ ኢትዮጵያውያን ነን ስንል በኖርነው ዘንድ እንኳ ኢትዮጵያውነታችን ነውረኛ አሳብ ስለሆነብን፥ ከኢትዮጵያውነታችን ይልቅ ጎጣችንን መንደራችንን ጎሳችንን ዘራችንን መቍጠር ስለጀመርን ኢትዮጵያዊን ከሰው የሚቆጥረው የለም። 

ኢትዮጵያዊነት በአደባባይ የወደቀው በአረብ አደባባይ አይደለም፤ በአረብ አደባባይስ ኢትዮጵያዊነትን ለመግደል፥ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ለዘመናት ተጎንጉኖ፥ ተቋጥሮ ተፈቶ አልተሳካም ነበር። የአልጄሪያው ደባ፥ የሊቢያው ስጦታ፥ የሳውዲው ስለት፥ የደማስቆው ፖለቲካ ምንም አላመጣም ነበር። 
ኢትዮጵያውያዊነት የወደቀው በራሷ በኢትዮጵያ አደባባዮች ላይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ክብር ሳይሆን መርገም እንደሆነ የተነገረው በራሷ አደባባይ ነው። ወጣቱ በገዛ አገሩ ተስፋውን ሲያጣ አብሮ የመኖር ተስፋን ሲያጣ፥ የማደግ ተስፋን ሲያጣ፥ በገዛ አገሩ የዝግታ ሞት ከሚሞት፥ በሶማሊያ በረሃዎች በረሃብ ተቃጥሎ መውደቅ ይሻለኛል አለ። ጠኔ በገደለው አንጀቱ በገዛ አገሩ የሞት ሞትን ከምሞት በሲናይ በረሃዎች በበድዊኖች ተገድሎ ሬሳው ለሽያጭ እንዲቀርብ አደረገው። ወደየመን ለመሻገር ሲሉ ቀይ ባሕር የበላቸው ወደ ማልታ፥ ወደስፔይን፥ ወደጣልያን ለመሻገር የሜዲተራኒያን ባሕር የበላቸው ስንቶች ናቸው።  
ዛሬ ጥቂት የዩቱዩብ ቪዲዮዎች ስሜታችንን መቀስቀሳቸው መልካም ነው። ግን ይህ የተቀሰቀሰው ስሜታችን ሊጠይቀው የሚገባው ነገር ይህ ነው። በገዛ ደጃፋችን የወደቀው ኢትዮጵያዊነታችን የሚነሣው መቼ ነው?  ኢትዮጵያዊው በብሔሩ፥ በጎሳው ወይም በመንደሩ ሳይሆን በሰውነቱ ክብር የምንሰጠው መቼ ነው? ይህ በሽታ ሁላችንም ላይ ከላይ እስከታች የተጋባብን ነን። 

ለገዛ ወገናችን፥ ለዚያ  ለአንዱ ኢትዮጵያዊ ሰብአዊ ክብር መስጠት እስካልቻልን ድረስ ለብዙዎቹ ክብር መስጠት አንችልም። እኛው ለራሳችን ክብር ካልሰጠን ማንም ክብር ሊሰጠን አይችልም። ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ . . . እንዲሉ አባቶች። 

No comments:

Post a Comment