(ክፍል አንድ)
ከሰሞኑ ከየአቅጣጫው የሚሰማው የወገኖቻችን እንግልት ያስታወሰኝ የራሔልን ታሪክ ነው። መተርጉማን አባቶቻችን በትውፊት እንደሚነግሩን ከሆነ ራሔል በግብፅ በስደት ዓለም የነበረች እስራኤላዊት ነበረች። ነፍሰጡር ሆና ሳለ ለፒራሚድ መሥሪያ የሚሆን ጡብ እንድትሠራ የታዘዘች ሴት ነበረች። ለጡብ የሚሆነውን ጭቃ እየረገጠች ሳለች ምጥ መጣባት፤ አሠሪዎቿ አታቁሚ አሉአት። ደም ሲፈሳት አታቁሚ እንዲያውም ደሙ ጡቡን ያበረታዋል አሏት። መንታ ልጆች ከማኅፀኗ ወትተው ከጭቃው ወደቁ፤ አታቁሚ አብረሽ ከጭቃው ጋር አብረሽ ርገጫቸው አሉአት። የዚያን ጊዜ ወደሰማይ ቀና ብላ « ኢሃሎኑ በዝ ሰማይ አምላከ እሥራኤል፤ በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምን?» ብላ እንባዋን ወደሰማይ ረጨች። የእግዚአብሔርን ሕልውና የመጠራጠር ጥያቄ ሳይሆን « ይህን ግፍ አትመለከትምን? አታይምን? ለማለት ነው።
እግዚአብሔር አየ ተመለከተ፤ እሥራኤላውያንንም ከባርነት ነጻ አወጣቸው። ልበ አምላክ ዳዊት እንደተናገረው፥ እስራኤላውያንን « በብርና በወርቅ አወጣቸው።» መዝ 104፥ 37። ነገር ግን ምንም እንኳ ከባርነት ነጻ ቢወጡም፥ የልባቸው ደንዳናነትና እግዚአብሔርን ለመስማት እምቢ ማለታቸው የመከራቸውን ቀን አረዘመው። በአርባ ቀን የሚገቡባትን ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ለመውረስ አርባ ዓመት ፈጀባቸው። የሚበዙቱ ባለማመናቸው ጠንቅ በምድረ በዳ ወድቀው ቀሩ።
በሕዝቤ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍና በደል፥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለስደት መዳረጋቸውና እርሱን ተከትሎ እየደረሰባቸው ያለው ሰቆቃ፥ እንዲሁም አገራችን ያለችበት ፈርጀ ብዙ የሆኑ መስቀለኛ መንገዶችን ሳስብ የጠየቅሁት ይህንን ነበር፦ ፥ መከራችን ለምን ረዘመ? መከራችንን ያረዘምነው እኛ እንሆንን? ከሆነስ ለመሆኑ መከራችንንስ የምናረዝመው እስከመቼ ነው? እስከመቼስ ነው በዚህ ዓይነት ሁኔታ የምንኖረው?
ከዚህ በታችን የምንመለከታቸው ነጥቦች እንደእኔ እምነት መከራችንን እንዲረዝም አድርገዋል የምላቸው ነጥቦች ናቸው። የአንድ ሕዝብን ለዚያውም ረጅም ታሪክና ውስብስብ ችግሮች ያሉበትን ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮች በዚህ አጭር ጽሑፍ በዝርዝር ለመግለጥ ከባድ ነው። ሆኖም ግን እነዚህ ነጥቦች ነጥቦች ዋና ዋና የሆኑትን ችግሮቻችንን ይዳስሳሉ ለበለጠ ውይይትም ያነሣሡናል ብዬ አምናለሁ።
1. ያለፈ ታሪካችን እስረኞች መሆናችን
የሃይማኖት ሰው እንደመሆኔ ታሪክ በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ታላቅ ሥፍራ አስተውላለሁ። ነገር ግን ታሪክ የምንማርበት እንጂ በትምክህትም ሆነ በጥላቻ የምንታሰርበት አይደለም። ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት ወደኋላ ዘወር ብለን ብንመለከት፥ ማኅበራዊ ውይይታችን በአብዛኛው የሚያጠነጥነው አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ሳይሆን ባለፈው ነገራችን ላይ ነው። ከሁሉም የሚያሳዝነው ይህ ዓይነቱ ዕይታ በጣም ተጽእኖ ከማድረጉ የተነሣ ስለ ዛሬዋ ኢትዮጵያ « ትንታኔ» የሚሰጠው በዚሁ የትናንት ማንነት ላይ ነው።
ይህ የያለፈ ታሪካችን እስረኞች የመሆናችን ነገር የተመሠረተው በሁለት ተቃራኒና ጽንፈኛ እይታዎች ላይ ነው። እነዚህ ጽንፈኛ እይታዎች በተቃራኒ ይቁሙ እንጂ አደገኝነታቸው በብዙ መንገድ ያመሳስላቸዋል።
እንደኛው ከዛሬ ኃላፊነትና የትውልድ ጥያቄ ለማምለጥ በትላንት ታሪካችን ውስጥ የመሸሸግ አካሄድ ነው። በእንደዚህ አካሄድ የሚሄድ ሰው የኔ ብሎ የሚጠቅሰው ትላንት ከትናንት ወዲያ አባቶቹ የሠሩትን ነገር ነው። የዛሬውን ሲጠየቅ፥ ወይም ጊዜና ትውልድ ሲጠይቀው ታሪኩን ማምለጫ ያደርገዋል፤ ከትናንቱ ተምሮ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ደግሞ ቆሞ መመለስ አቅም ስለሚያንሰው [ስላልጣረ]፥ የአቋራጭ መንገድ ያደረገው ወጉን ነው። የትናንቱን የአባቶቹን ታሪክ መተረኩን ነው። አባቶቻችን በታሪካቸውና በጊዜያቸው መልካም አድርገዋል። የተሳሳቱበትም ጊዜ አለ። በዚህ ተመስግነውበታል ተወቅሰውበታል። አንተ ደግሞ በአንተነትህ በጊዜህና በታሪክህ ተመስገንበት ተወቀስበት ስትሉት ቶሎ ብሎ የቀድሞውን ጥግ ያደርጋል። እንዳይወቀስ። ምክንያቱም በዚህ በእርሱ አስተያየት የትናንቶቹ አይተቹም አይወቀሱም፤ የትናንቱን ታሪክ የሚያየው ለትምክህት ሌላውን ለመናቅና አሳንሶ ለማየት እንጂ ለትምህርት ስላይደለ፥ ስህተቱንና ትክክለኛውን ታሪክ ለይቶ አያውቀውም። ታሪኩን ዶግማ አድርጎ ስለያዘው እንዳለ መቀበልን ታላቅ ተግባር አድርጎ መያዝ ብቻ ሳይሆን በትናንት ላይ ጥያቄ የሚያነሣውን በኑፋቄ ይከሰዋል። የአባቶቹን ታሪክና ወግ እንደረሳ አድርጎ።
ይህ በእኛ ውስጥ ብዙ ይታያል። ታሪክ የመውደዳችን ያህል ታሪካችን የኋልዮሽ የወሰደን ይመስለኛል። አፍሪካ አሜሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንን በንቀት ለማየት የኢትዮጵያን ታሪክ የሚጠቅሱ አጋጥመውኛል። በመካከላችን እንኳ እርስ በእርስ ለመከባበርና ለመቀባበል ታሪክ ገደብ የሆነብን ሞልተናል። ስለዚህ ጉዳይ በሰፊው ስለምናትት ለጊዜው እናቁም።
ከዚህ ጽንፍ ወደተቃራኒው ጽንፍ ስንሄድ ደግሞ የምናገኘውፍ ሁለተኛው ጽንፋዊ እይታ ያለፈ ታሪካችን እስረኛ ከመሆኑ የተነሣ የዛሬ ሁለት መቶ ዓመት ተሠራ በሚለው ግፍ ደረት የሚያስደቃውና ሙሾ የሚያስወርደው ክፍል ነው። አሁንም ይህ ክፍል የዛሬውን ማንነቱን በትናንንቱ ታሪክ ውስጥ ያስቀመጠ ብቻ ሳይሆን ከትናንት አገኘሁት ባለው ታሪክ፥ የምሬትና የጥላቻ ታሪክ ዛሬን መቅረጽ የሚፈልግ ወገን ነው። ስለዛሬ ተናገር ሲባል የሚጀምረው « አፄው. . . አማራ. . . ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን» አደረሱት የሚላቸው በደሎች በመዘርዘር ነው። ገና ከጅምሩ የትናንቱን ታሪክ እጅግ በከረረ ጥላቻ ስለሚያየው በትናንቱ ውስጥ የነበሩትን መልካም ነገሮች ለማየት ፈቃደኛ አይደለም። ከዚህ በላይም በትናንቱ ታሪክ ውስጥ ዓይነተኛ ሚና የነበራቸው አካላት ወራሾች ናቸው የሚላቸውን ሕዝቦች እና ተቋሞች ዋነኛ ጠላቶቹ ናቸው።እነዚህ ተቋሞችና ሕዝቦች ዛሬ ያላቸውን ሁኔታ ከግምት ማስገባት ለእርሱ ማመቻመች መስሎ ስለሚታየው ቆም ብሎ ለማየት ጊዜ የለውም። በታሪክ እንደምናየው ይህ ዓይነቱ አደገኛ የሆነ የታሪክ አተረጓጎም ሁል ጊዜ የሚያደርሰው ወደ አስፈሪ ድምዳሜ ነው። የሕልውናዬ መሠረት የእነርሱ መጥፋት ነው ወደሚል። ናዚ ጀርመን በጀርመን አይሁዶች ላይ፥ ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ ያደረሱት እልቂት የመነጨው ከዚህ ነው።
የእነዚህ ሁለት ጽንፋዊ ዕይታዎች ተመሳሳይነት ምንድነው? አንደኛ ታሪክን ግልብ በሆነ እይታ ለመተርጎም መሞከራቸው ነው። ሁለቱም ክፍሎች ታሪካዊ አተረጓጎም ላይ ላዩን ስለሆነ ከታሪክ የሚማሩበትን በታሪካቸውም ራሳቸውን የሚወቅሱበትን ነገር አይጨብጡበትም። ይህ ወደ ሁለተኛው ተመሳሳይነታቸው ይመራናል። ሁለቱም ጽንፋዊ ዕይታዎች ታሪክን መሸሸጊያ ያደረጉት ከዛሬ ለመሸሽ ነው። አንደኛው ዛሬን ለመሸሽ ታሪክን ትምክህት ሲያደርግ ሌላው ደግሞ ዛሬን ለመሸሽ ታሪክን መክሰሻ ያደርጋል።
++++++++++++++
ባለፈው ዘመን ጥፋት አልነበረም አንልም። የኢትዮጵያ ታሪክን በማስተዋል ያነበበ ሰው እንደሚገነዘበው፥ ባለፉት የአገራችን ታሪኮች ብዙ አሳዛኝ ነገሮች ተከናውነዋል። በባርያ ንግድ የገዛ ወገናችንን ሸጠናል። ፋሺስት ጣልያን በመንግሥታቱ ድርጅት አገራችን ቅኝ ለማድረግ የሞገተው ይህን ድካማችንን ጥግ አድርጎ ነው። ይህን የከፋ ሁኔታ ለማስወገድ፥ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ እስከ አጼ ኃይለ ሥላሴ ድረስ የኢትዮጵያ መሪዎች የባሪያ ንግድን ለማስወገድ ያደረጉትን ጥረት ማስታወሱ ይበቃል።
ባለፈው ዘመን ሙያ እንደወንጀል ተቆጥሮ ባለሙያነት ጋብቻን የሚከለክል ነበር። ጸሐፊው ደብተራ ወይም ጠንቋይ ተብሎ ስለሚንቋሸሽ የአገር ታሪክን ጽፎ ለትውልድ የሚያስተላልፍ ሰው ማግኘት እንደ ብርቅ ነበር። ብረቱን የሚያነጥረውን ቆዳውን የሚዳምጠውን ፋቂና ቀጥቃጭ ብለነው ልጆቹን የፋቂና የቀጥቃጭ ልጅ ብለነው ፈጠራንና ግኝትን አፍነነዋል።
በሕዝቦች መካከልም ባለፈው ታሪካችን ግጭት ነበር። ግጭቶች በተለያዩ መንገዶች ይፈጠራሉ። የፖለቲካ ግጭቶች አሉ። መንግሥት ለአገዛዜ ይጠቅመኛል ብሎ ያሰበውን ለማድረግ ሲሞክር ተቃውሞ ይነሣል፤ ጦርነት ይከፈታል ። አንዳንድ ጊዜም ግጭቱ ሃይማኖታዊ ወይም ጎሳዊ መልክ ይኖረዋል። አንዳንድ ጊዜ ግጭቱ የኢኮኖሚ ይሆናል። የሕዝብ ከቦታ ቦታ ዝውውርንና መስፋፋትን ተከትሎ ግጭት ይፈጠራል። ባለፉት የአገራችን ታሪኮች ይህ አይነቱ ግጭት ነበረ። ዛሬም በአርብቶ አደርነት (ዘላንነት) በሚተዳደረው ሕዝባችን መካከል በግጦሽ መሬት ምክንያት የሚፈጠረውን ግጭትና የሰውና የንብረት ውድመት ስንመለከት ያለፈውን የሕዝቦች ግጭት በጥንቃቄ እንድናጠና ያደርገናል።
ስለ ታሪክ አተረጓጎም የታሪክ ባለሙያዎች የሚሉትን እዚህ ማተት ባያስፈልግም ነገር ግን ከላይ ባየናቸው በሁለቱም እይታዎች ውስጥ ያለው ታላቁ ድካም ታሪክን በዛሬው ማነታችን አውድ ( context ) ለመተርጎም አለመሞከራቸው ነው። ይህ ዓይነቱ የተጣመመ የታሪክ አመለካከት ዛሬ የሚታየው አልተማረም በምንለው ሕዝባችን መካከል ሳይሆን፥ በዕውቀት ማማችን ላይ ተቀምጠን ሕዝባችንን እንመራዋለን በምንለው ነው። ሕዝባችንማ ያለፈውን ድካምም ሆነ ብርታት አብሮ አልፎ ዛሬ ያለችውን አገር አስረክቦናል። ያስረከበን መንግሥት ሳይሆን ሕዝብ ነው።
ታሪክን ከመንግሥት አንጻር ሳይሆን ከሕዝብ አንጻር ማጥናት ከብዙ ስሕተት ያድናል። አጼ ምኒልክን ረግሞ ግራኝ መሐመድን ነጻ አውጪ ማድረግ የሚመጣውም ከዚህ ታሪክን ከመንግሥት አንጻር ከመመልከት የተሳሳተ አካሄድ ነው። ታሪካችንን ከመንግሥት አንጻር ካየነው አንዳችን ተቃዋሚ አንዳችን ደጋፊ ስለምንሆን አንዱን አጽድቀን አንዱን መኮነናችን የማይቀር ነው። የአንድ ጸሐፊ አገላለጥን ልጠቀምና፥ « እግሩ የት አንደሚያልቅና አፈሩ የት እንደሚጀምር» የማይታወቀውን አፈር ለብሶ አፈር የመሰለውን ደሃ ገበሬ ፥ « የገዢው መደብ፥ ነህ » እያልን በወጣን በገባን መጠን የምንረግመው ከዚህ ቀላል ከሚመስል ነገር ግን እጅግ አደገኛ ከሆነ የታሪክ « ትንታኔ» ስለምንጀምር ነው። ታሪካችንን ከሕዝብ ዛሬ ላይ ቆመን ስንጀምር ግን አንድ መሠረታዊ ነገርን እንገነዘባለን። ይህ ሕዝብ ችግርም ደስታም አንድ አድርጎት ዛሬን በተስፋ ያለ ሕዝብ ነው። በእኛ ትንታኔ ያን ተስፋውን አንውሰድበት። ተስፋ የሌለው ሕዝብ ከማየት በላይ የሚያስፈራ ነገር የለምና።
(ይቀጥላል)
Such a great article it is. Ewket, LeEdget; Haimanot, Le Ewnet mallet endih naw.
ReplyDeleteDiagnostic treatment ylutal. Identify the cause, then find its remedy.
It is a good start look fore ward to read the next part. thx
Great article....waiting for the next part.
ReplyDelete