በዓለት ላይ የተሠራው ቤት
ዶክተር ሊሊያን አልፊ
ትርጉም ቀሲስ መልአኩ ባወቀ
ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም። ማቴ 7፥25
አንድ ቀን ማለዳ፥ ከእንቅልፋችሁ ስትነሱ፥ በዓለም ላይ እጅግ የጸና መሠረት ያለው ነገር ከቦታው ጠፍቶ ልታገኙት ትችላላችሁ። ሂሮሺማ እንዳልነበረ ሆኖአል። የሶቪየት ኅብረት ተበታትኖአል። የበርሊን ግንብ ተደርምሶአል። የኒው ዮርኩ መንታ ሕንፃ ፈርሶአል። ብዙ ከተሞች በእሳተ ገሞራ፥ በውኃ መጥለቅለቅና በመሬት መንቀጥቀጥ እንዳልነበሩ ሆነዋል። የምንወዳቸውን ባልጠበቅነው መንገድ አጥተናቸዋል።
ነገር ግን አንድ ቀን ማለዳ፥ ከእንቅልፋችሁ ስትነቁ ኢየሱስ የሌለበት ቀን አጋጥሞአችኋል? በጭራሽ!! እርሱ በዘመናት የሸመገለ ዓለታችን ነው። መንግሥታት ይጠፋሉ፤ እርሱ ግን « ትናንትና፥ ዛሬም፥ ለዘላለም ያው ነው» እርሱ ቀናችንን ሁሉ ከእኛ ጋር ነው፤ ፀሐይ ይሁን ዝናብ፥ በጎ ይሁን ክፉ፥ በጤና ይሁን በሕመም፥ በሠርግ ይሁን በቀብር፥ በደስታ ይሁን በሐዘን፥ በቀን ይሁን በሌሊት፥ በዚህ ሕይወት ይሁን በሚመጣው ሕይወት እርሱ ይመጣል። ልንገፋ እንችላለን፤ የምንወዳቸውን ልናጣ እንችላለን፤ ነገር ግን « በሚነደው የእቶኑ እሳት» ውስጥ እንኳ እርሱ ከእኛ ጋር ነው።
ብዙ ቤቶችን በአሸዋ ላይ ገንብተናል። ብዙ ቤቶችን በአሸዋ ላይ መገንባታችንን ቀጥለናል። ለእነዚህ ቤቶች የተጠበቀላቸው አጠቃላይ ጥፋትና ውድመት ነው። በቅጽበት ሕይወት ሊለወጥ ይችላል፤ በዚያን ጊዜ የሚቀረው በዓለት ላይ የተሠራው ቤት ነው።
No comments:
Post a Comment