« ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፥ መከራን ተቀበል፥ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፥ አገልግሎትህን ፈጽም።» 2 ጢሞቴዎስ 4፥2-5
ቅዱስ ጳውሎስ ከልጅነት እስከ እውቀት በወንጌል ኮትኩቶ ያሳደገውን መንፈሳዊ ልጁን ጢሞቴዎስን የወንጌል አደራውን እንዴት መፈጸም እንዳለበት በአጽንዖት የመከረው የአገልግሎትህ ግብ ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት ማቅረብ ነው።
ሕይወት የሚገኝበት ትምህርት ማለት ምን ማለት ነው? በቅዱስ ጳውሎስም ሆነ የወንጌልን አደራ በሰጠው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት መሠረት ሕይወት የሚገኝበት ትምህርት ማለት የተቀበሉት ትምህርት የሰሚዎችን ሕይወት ሲለውጥና እግዚአብሔርን ወደመምሰል ሲያመጣ ነው። ጌታ የመንግሥቱን ወንጌል ለማስተማር መጀመሪያ ያደረገው « መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» የሚለውን ትምህርት ነው። ጌታ « ንስሐ ግቡ » ሲል ሕይወታችሁን ወደ እግዚአብሔር መልሱ የኑሮ አካሄድ ለውጥ አድርጉ ለማለት ነው። በጠፋው ልጅ ታሪክ ውስጥም የጠፋው ልጅ በንስሐ ወደ አባቱ መመለሱን የሚያመለክተው ቃል « ወደ ልቡ ተመልሶ» በሚል ሐረግ ተገልጦአል።
ሐዋርያው ለመጨረሻ ጊዜ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት መልእክት ያስጨነቀው ነገር ቢኖር፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች ሕይወት የሚገኝበትን ማለትም የሕይወት ለውጥን የሚጋብዝን ትምህርት የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል የሚል ነው። ይህ በእኛ ዘመን ተከናውኖ ይሆን? የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት የሚገኝበት ትምህርትን ነው እያስተማረች ያለችው?
እጅግ ጠንከር ያለ ቢመስልም ዛሬ ያለንበት እውነታው ይህ ነው። በቤተ ክርስቲያን አደባባዮች ፍቅር የለም፤ በአገልጋዮቿ መካከል ሰላም የለም። ኃጢአት ከመቅደሷ ጀምሮ እስከአደባባዮቿ ነግሶአል። እግዚአብሔርን መፍራት ሞኝነት መስሎ የታየበት፥ የአፍኒንና የፊንሐስ የድፍረት ኃጢአት የአግልግሎት ኩራት የሆነበት፥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲራብ በማድረግ በተለያዩ ማታለያዎች ማወናበድ ሥራዬ ተብሎ የተያዘበት ጊዜ ላይ ነን። በዓለም አደባባይ፥ በየፍርድ ቤቱ የምንከራከር፤ ገበናችንን በየጋዜጣውና በየቴሌቪዢኑ የምናዝረከርክ፥ የሚወገዙልንን ወይም የሚወነጀሉልንን ወይም ገበናቸውን የምናጋልጣቸውን ወንድሞቻችንን፥ እህቶቻችንንን፥ ጳጳሳቶቻችንንና ካህናቶቻችንንን ስም ዝርዝር ይዘን ከቦታ ቦታ የምንከራተት ነን። በዚህ ሁሉ ግን እያስተማርን ነው። በስብከታችን እያስተማርን ነው፤ በመዝሙራችን እያስተማርን ነው። በማኅሌታችን እያስተማርን ነው።
ሕይወት የማይገኝበት ትምህርት ምን ዓይነት ነው? ሕይወት የማይገኝበት ትምህርት የምንለው በክርስቲያናዊ አካሄዳችን ላይ አንዳችም ለውጥ የማያመጣ ሲሆን ነው። ወደ ንስሐ የማያመጣን ከሆነ፥ በፍቅር አንድ የማያደርገን ከሆነ፥ ለሰላምና ለይቅርታ የማይገፋፋን ከሆነ ያ ትምህርት ሕይወት የማይገኝበት ትምህርት ሊሆን ነው። እኛ ካልፈወስነው።
ቤተ ክርስቲያን ማለትም እኛ በዚህ ዘመን ልንጠይቅ የሚገባን ነገር አለ። አንድ የሚያደርገን ነገር ምንድነው? አንዳንዶች ላንቃቸው እስኪተረተር አየር እስኪያጥራቸው ድረስ ጩኸው የሚመልሱት « አንድ የሚያደርገን የቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ (ዶክትሪኗ) ነው» ይሉ ይሆናል። የኔ ጥያቄ ይህ ነው፤ ይህ ትምህርት ሕይወትን ገልጦአል ወይ? ይህ ትምህርት፥ ይህ የምንናገረው፥ የምንሰብከው ትምህርት ሕይወትን ገልጦአል ወይ? ማለትም አንድ አድርጎናል ወይ? ሰላምን ሰጥቶናል ወይ ? አፋቅሮናል ወይ?
በዚህ ዘመን የትምህርት እንጂ የሕይወት አንድነት ስለሌለን በሕይወት የሚገለጠውን ክርስቶስን ለዓለም ለማሳየት አልቻልንም። ጉሮሮአችን እስኪዘጋ ድረስ ክርስቲያኖች መሆናችንን፥ የክርስቶስ ተልእኮ የተሰጠን መሆኑን እየተናገርን ነው። ዓለም ግን በእኛ ውስጥ ክርስቶስን ሊያይ ስላልቻለ ራሱን እየነቀነቀ ወደ ጥፋት ጎዳና እየሄደ ነው።
የትምህርት እንጂ የሕይወት አንድነት ስለሌለን፥ በሕይወታችን ክርስቶስን ማሳየት ቢያቅተን በየጉራንጉሩ ተአምራት እየፈለግን ነው። ተአምራቶች ሕይወትን የሚያጸኑ እንጂ ሕይወትን የሚያመጡ አይደሉም፤ ከጥፋትም አያድኑም።
ከአበው የመጣ ቢሆንም እንኳ በአንዳንድ ታዋቂ ሰባክያን ተደጋግሞ የሚነገር ነገር ግን በጥንቃቄ ልናየው የሚገባን ነገር አለ። አነጋገሩ እንዲህ የሚል ነው። አባቶች አንድን መጽሐፍ ደገኛ (ታላቅ መንፈሳዊ) መጽሐፍ ነው ብለው የሚቀበሉት፥ በእሳት አግብተው ሳይቃጠል ሲቀር፥ ወይም በውኃ ቢጥሉት ሳይረጥብ ቢወጣ፥ ወይም ደግሞ በበሽተኛ ላይ ቢጥሉ በሽተኛውን ቢፈውሰው ነው የሚል ነው። መልካም አባባል ነው። ነገር ግን ይህ ሁሉ መመዘኛ ከንቱ የሚሆንበት ጊዜ ይመጣል። መመዘኛው አንድ ነገር ብቻ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ሕይወት።
ጌታ በተራራው ስብከት ላይ ስለዚህ ሲናገር « ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።በዚያ ቀን ብዙዎች ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።» ብሎአል። ማቴዎስ 7፥20 - 23
የቃላት ውበት፥ « ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ» ፥ ወይም የተአምራት ብዛት « ትንቢት መናገር፥ አጋንንት ማውጣት፥ ተአምራት ማድረግ » በጌታ ዘንድ መታወቅን አላመጣም። ነገር ግን ጌታ በተአምራቱ መካከል፥ በዝማሬው መካከል፥ በቅዳሴው መካከል፥ በስብከቱ መካከል፥ በሕዝቡ ብዛት መካከል አንድ ነገር ይፈልጋል። የሕይወት ፍሬን።
ጌታ ሆይ አንተ በገለጥክልን ቅዱሳን ሐዋርያት እና እነርሱን ተከትለው የተነሱት አባቶቻችንና እናቶቻችን ባስተማሩን የሕይወት መንገድ ላይ ሆነን በሕይወታችን አንተን እንድንገልጥ እርዳን አሜን።
No comments:
Post a Comment