በመላው ዓለም የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሳውድ አረቢያ ለሚሰቃዩት እኅቶቹና ወንድሞቹ ድምጹን ሲያሰማ፥ በአውሮፓ አንድ ታሪካዊ ዝክር እየታሰበ ነው። በአውሮፓ አቆጣጠር ኖቬምበር 10 ቀን የተሰባበሩ መስተዋቶች ምሽት ወይም በጀርመንኛው Kristallnacht ይባላል። ይህ በናዚ ፓራሚሊተሪዎችና የናዚ ደጋፊዎች የተቀነባበረ ዘመቻ በጀርመንና በኦስትሪያ በሚገኙት አይሁድ ላይ ጥቃትና ድብደባ የተካሄደበት ምሽት 75ኛ ዓመት መታሰቢያ ነው።
በዚያች አስጨናቂ ምሽት ከ90 በላይ አይሁዶች የተገደሉ ሲሆን ከ30,000 በላይ የሚሆኑ ወደ ማሰቃያ ካምፖች ተወስደዋል። ይህን አሳዛኝ የሆነውን ታሪካዊ ምሽት ለማክበር ክርስቲያኖችና አይሁድ በጋራ ጸሎት አድርገዋል። በኢንግሊዝ አገር በዌስት ሚኒስተር አቤይ ለተሰበሰቡ ክርስቲያኖችና አይሁዶች ንግግር ያደረጉት ራባይ እንደተናገሩት ይህ ቀን መታሰብ ያለበት በተስፋ መልእክት ነው ብለዋል።
እኚ ራባይ ሲናገሩ « ያን ሽብር፥ ግድያና፥ ውድመት፥ የወላጅ የቤተሰብ የጓደኛ እጦት ስናስብ፥ ዛሬ ክርስቲያኖችና አይሁድ በጋራ ሆነን ተራ የሆኑ ሰዎች አስደናቂ ነገር ማድረግ እንደሚችሉ በማሰብ እናክብር፤. . . እኛ ዛሬ በሕይወት ያለነው በመላው ዓለም ላይ ስለሕይወታቸው ፈርተው ያሉትን ልንረዳ ጠመዝማዛውን የቢሮክራሲ ሰንሰለት አልፈን አንድ ነፍስ እንኳ ብንረዳ ብለዋል። በትውፊታችን እንደተጻፈው አንድ ነፍስ ያዳነ አለምን ሁሉ እንዳዳነ ነው» ብለዋል።
እውነት ነው፤ ራባዩ ያነሱት የአይሁድ ትውፊት ላይ የአንድ ሰውን ሕይወት የገደለ የሰው ዘርን በሙሉ እንደገደለ እንደሚቆጠርም ይነገራል።
ዛሬ ይህን ታሪካዊ ምሽት ስናስብና 6 ሚሊየን የሚሆኑ አይሁድ ላይ የደረሰውን ሰቆቃ ስናስብ ዛሬም ለአንድ ሰው ሰብአዊ ሕይወት፥ መብትና ነጻነት የመቆም ታላቅ ኃላፊነት አንዳለብን ማስታወስ ይገባናል።
ይህ አሳዛኝ ድርጊት በአገሩ ላይ ሲደረግ በዝምታ በመመልከቱ ጸጸት ውስጥ የገባው የጀርመን ሉተራን ቄስ ያለውን እዚህ ላይ ማስተዋል አለብን። « መጀመሪያ ወደ ኮሚንስቶች መጡ፥ እኔ ኮሚንስት ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። ቀጥሎ ወደ ሠራተኛ ማኅበራት መጡ የሠራተኛ ማኅበራት አባል ስላልሆንኩ ዝም አልኩ። ወደ አይሁድ መጡ አይሁድ ስላልሆንኩ ምንም አልተናገርኩም። በመጨረሻ ወደ እኔ መጡ። ስለ እኔ የሚናገርልኝ አንድም የተረፈ አልነበረም።
ምንጭ፦Religion News Service
No comments:
Post a Comment