Friday, October 24, 2014

በክርስቶስ መረጠን

Read in PDF

 በክርስቶስ መረጠን። 
« ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።» ኤፌሶን 1፥4 ይህ እግዚአብሔር እኛን የመረጠበት ጸጋ የተከናወነው በክርስቶስ ነው። እግዚአብሔር አስቀድሞ ሲፈጥረን በእርሱ አርዓያና አምሳል ነበር። (ዘፍ 1፥27) ሆኖም ግን በአንዱ በአዳም በደል ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ሲገባ፥ በሰው ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን አርዓያና አምሳል አደበዘዘው፥ አጎደፈው፥ አበላሸው። ወደፊት በኤፌሶን ምዕራፍ ሁለት ጥናታችን በሰፊው እንደምናየው ሰው በእግዚአብሔር ቍጣ ሥር ወደቀ። ይህ የሰው ውድቀት ከእግዚአብሔር የተሰወረ ነውን? እግዚአብሔር የማያውቀው ነውን? አይደለም። እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ወይ ዓለም ሳይፈጠር የሰውን ድካምና ውድቀት ያውቅ ነበር። ሰው በድካሙ ከገባበት ውድቀት የሚድንበትንም መንገድ አዘጋጀ። በመሆኑም በአንዱ ሰው የገባውን ሞት ድል ያደርገው ዘንድ አንዱን ልጁን ዓለምን ለማዳን ላከው። በሥላሴ ምክር የተዘጋጀው የመዳን መንገድ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው በክርስቶስ መረጠን ሲል እግዚአብሔር እኛን የእርሱ ሊያደርገን ያዘጋጀው መንገድ ክርስቶስ መሆኑን ለማመልከት ነው። 

የወልድ እግዚአብሔር ሰው መሆን አዳም ከወደቀ በኋላ የታቀደና የተወሰነ አይደለም፤ዓለም ሳይፈጠር የተወሰነ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ስብከቱ ላይ ግልጥ እንዳደረገው፥ ልክ እንደእኛ ምርጫ ፥የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ሞትና ትንሣኤ ዓለም ሳይፈጠር በእግዚአብሔር የታቀደ እና የተወሰነ ነው። ሐዋርያው በዚያ ለተሰበሰቡ በሺ ለሚቆጠሩ ሰዎች ያለው ይህን ነው። «የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።» ሐዋ 2፥22-24 ። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው፥ ክርስቶስ ለእኛ መዳን መሥዋዕት እንዲሆን ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የተዘጋጀ መሆኑን ነው። 

Thursday, October 23, 2014

በፍቅር እንሆን ዘንድ መረጠን

Read in PDF

« ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።» ኤፌሶን 1፥4። 

በፍቅር የተሞላ አምላክ እኛን የመረጠን በፍቅሩ ነው። በዘላለም ፍቅሩ ነው። ወንጌላውያኑ ተባብረው እንዲህ ይላሉ። « ወደ ተራራም ወጣ፥ ራሱም የወደዳቸውን ወደ እርሱ ጠራ፥ ወደ እርሱም ሄዱ። ማርቆስ 3፥13። ዮሐንስ ደግሞ እንዲህ ይላል « ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። ዮሐንስ 13፥1። የመረጠን በፍቅሩ ነው።
ይህ ቃል በሚቀጥለው ቍጥር በሰፊው እንደምናየው ሰፊ አንድምታ አለው። ፍቅሩ ልጁ ነው። እግዚአብሔር እኛን ያድን ዘንድ ከፈጠረው ፍጥረት መካከል አንዱን አልላከም። የላከው የሚወደውን፥ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድ ልጁን ነው። በቅዳሴያችን፥ በማኅሌታችን  «በፍቁር ወልድከ በውድ ልጅህ» እያልን የምንጸልየው የምናዜመው፥ የምናመሰግነው ለዚህ ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅሩን የገለጠው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ነውና።   
እንደገና የመረጠን በዚሁ ፍቅር እንመላለስ ዘንድ ነው። « በፍቅሬ ኑሩ» የእርሱ አቢይ ትእዛዝ ነው። ይህ ማለት እግዚአብሔር አለም ሳይፈጠር ላቀደልን ታላቅ ዓላማ ልጁን ወደመምሰል መድረስ የምንችለው በእርሱ ፍቅር ስንኖር ነው። ፍቅሩ የሕይወታችን የኑሮአችን ማዕከል ሲሆን ነው። «በፍቅር የሚሰራ እምነት» የሰጠንም ለዚህ ነው። እርሱን ሳንወድ ወይም በእርሱ ፍቅር ሳንኖር እርሱን ደስ የሚያሰኝ ነገር ልንሠራ አንችልም፤ በመላእክት ልሳን ብንናገር፥ ያለንን ሁሉ ለድሆች ብንመጸውት፥ ሰውነታችንን ለእሳት አሳልፈን ብንሰጥ፥ ተራራንን የሚያንቀሳቅስ እምነት ቢኖረን ፍቅር ከሌለን ከንቱ ነን። ( 1 ቆሮ 13) 

ለቅድስና የመረጠን ጌታ በፍቅር እንድንኖር መርጦናል። አለምክንያት አይደለም ቅድስናና ፍቅር  አብረው ይሄዳሉ። በፍቅር ውስጥ ያለ ሰው የሚያስበው በንጽሕና ራሱን ለሚያፈቅረው ማቅረብን ነው። ፍቅር ሳይኖር ቅድስናን ማሰብ አይቻልም። ሊኖርም አይችልም። ፍቅር በሌለበት ሕይወትና ቤት ውስጥ የመጀመሪያው የሚጠፋው ነገር ቅድስና ነው። እግዚአብሔርን ሳትወዱት በቅድስና መኖር አትችሉም። ወንድሞቻችንን ሳንወድ በቅድስና መኖር አንችልም። በፍቅር መኖርን ታላቅ የክርስትናችን መንገድ ማድረግ ያለብንም ለዚህ ነው። 

ብዙዎች ለእምነት ታላቅ ትኩረት እንሰጣለን የሚሉ፥ ከቤተ ክርስቲያን የማይጠፉ፥ በቅዳሴው፥ በማኅሌቱ፥ በማናቸውም ሥራ የሚተጉ፥ ፍቅር አልባ በሆነ ሕይወት ሲመላለሱ ይታያሉ። እነዚህን ሰዎች ቀረብ ብላችሁ ሕይወታቸውን ስትመለከቱ፥ የሚታገሉት ፍቅር አልባ በሆነ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ቅድስና አልባ በሆነም ሕይወት ነው። እንደገና እደግመዋለሁ። ፍቅር ከሕይወታችን ከቤታችን ሲወጣ ቅድስናም ይከተላል። ቅድስና በሌለበት ሕይወትም ፍቅር የለም፤ የቱንም ያህል « የፍቅር ቃላት» ይደርደር እንጂ፥ ቅድስና የሌለበት ሕይወት ፍቅር የለውም። ለዚህ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም ዙሪያ ገባውን ማየት ብቻ ነው የሚያስፈልገው። 


እኔና እናንተስ? በፍቅር በወደደን አምላክ ትእዛዝ ውስጥ ውስጥ ሆነን በእርሱ ፍቅር እየኖርን ነውን? ፍቅሩን የሕይወታችን ማዕከል አድርገነዋልን? በመስቀል ላይ ፍቅሩን የገለጠለን ጌታን ፍቅሩን፥ ውለታውን፥ ቸርነቱን በማሰብ ሕይወታችንን በእርሱ ላይ እንድናሳርፍ እግዚአብሔር ይርዳን። 

Wednesday, October 22, 2014

ለቅድስና መረጠን።

Read in PDF

«ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።» 
ኤፌሶን 1፥4 

የመረጠን በፊቱ ቅዱሳንና ነው የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ ነው። የመጀመሪያውን እንመልከት የመረጠን ቅዱሳን እንሆን ዘንድ ነው። ቅዱስ ማለት ልዩ ንጹሕ ክቡር ማለት ማለት ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ ነው። ልዩ ክቡር ንጹሕ ነው።  በነገራችን እግዚአብሔር መንገድ አይደለም በአዲስ ኪዳን የተከተለው። በብሉይ ኪዳንም እስራኤልን ሲመርጥ ያላት ይህን ነበር። «ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።» ዘሌዋውያን 19፥2  ሌዋውያንን ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ሲጠራቸው የቅድስና አዋጅን እንዲነግሩ በግንባራቸው ላይ « ቅድስና ለእግዚአብሔር» የሚል ጽሑፍ ያለበት አክሊል እንዲያደርጉ ነበር የነገራቸው።( ዘጸአት 39፥30 ።) በአጠቃላይ እግዚአብሔር እስራኤን የጠራት « ቅዱስ ሕዝብ»  እንድትሆን ነበር። 

በአዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔር አሳብ ይኸው ነው። የመረጠን በፊቱ ቅዱሳን እንድንሆን ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ ስለዚህ በሚገባ አስረግጦ ይነግረናል። «እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤» 1 ጴጥሮስ 2፥9።  ይህን የእግዚአብሔርን ባሕርይ የእኛ ማድረግ የሕይወታችን ነው። ክርስቲያናዊ ሕይወትም የምንለው ይህን ነው። ለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ « ትቀደሱ ዘንድ በብርቱ ፈልጉ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና» በማለት የተናገረው። ዕብራውያን 12፥14። 

እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ስንል እግዚአብሔር ብርሃን ነው፥ እግዚአብሔር ፍጹም ነው ማለታችን ነው። እግዚአብሔር ልዩ ክቡር ንጹሕ ነው።  ጨለማ በእርሱ ዘንድ የሌለበት አምላክ ነውና። ይህ የብርሃን ጌታ የቅድስና ሕይወት አሁን እንዳየነው በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ለእኛ ለልጆቹ ሰጥቶናል። የሚያሳዝነው ግን  እኛ ለቅድስና የተጠራን ልጆቹ ስለ ቅድስና ያለን አስተሳሰብ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ስለቅድስና ሕይወት ተሰምቶን ያውቃልን? ስለቅድስናችን ሕይወታችንን ለመመርመር ጊዜ ኖሮን ያውቃልን? ቅዱሳን እንድንሆን ልዩ ንጹሕ እንድንሆን እግዚአብሔር ሲጠራን፥ የእርሱ ብርሃንነት በልባችን እንዲያበራና ጨለማ ከእኛ እንዲርቅ ነው። የቅድስና ሕይወት  የልብ ንጽሕና፥ የልብ ብርሃንነት፥ በአሳብ፥ በፈቃድ የመለየት ነው። እግዚአብሔርን የማንገሥ ነገር ነው። በአእምሮ መታደስ ተለውጦ እግዚአብሔርን አክብሮ የመኖርን ሕይወት ነው የሚናገረው። ይህን ነው ቅድስና የምንለው። 

ጳውሎስ ግን በዚህ አያበቃም። የሚለን እግዚአብሔር የመረጠን ቅዱሳንና ነውር የሌለን እንድንሆን ነው። ቅድስና ( ሐጊዮስ) የውስጥ ነገር ነው። ያለ ነውር መኖር  በአፍአ ( በውጭ) ያለ ነገር ነው። በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት በቅድስናና ያለ ነውር የመኖር ሕይወት።  በብሉይ ኪዳን እንስሳው ለመሥዋዕት ከመቅረቡ በፊት በሚገባ መመርመር አለበት። ነውር ያለበት እንስሳ ለመሥዋዕትነት መቅረብ አይችልም ነበር። ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ጉድለት የሌለበት ከሁሉ የተመረጠውን ነበር።ያለነውር መኖር ማለት ምን ማለት ነው። በቅድስና ሕይወት ለእግዚአብሔር መሰጠት፥ በንጽሕና መኖር፥ ሕይወታችንን እንደፈቃዱ መምራት፥ በሰዎች ፊት ብርሃን መሆን ማለት ነው። ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ትእዛዝ ይህ ነው። በዓለም ፊት ብርሃን እንድትሆን፥ ጨው እንድትሆን ነው። 

ዛሬ  ቤተ ክርስቲያን (እኛ) በዚያ ውስጥ ነን ወይ? በአገልጋዮቿ መካከል ቅድስና አለ ወይ? በሕዝቦቿ መካከል ያ ቅድስና አለ ወይ? አንድ ታዋቂ የነገረ መለኮት የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቅ የተናገረውን እዚህ ጋ ልጥቀስ «  . . . በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያን ከዓለም የተለየ መሆን እንዳለበት ምንም ጥርጥር አልነበረውም። እንዲያውም ልዩነቱ ግልጥ ያለ ስለሆነ፥ ዓለም ሊገድለው ወይም ሊጠላው እንደሚችል ያውቅ ነበር። በዘመናዊው ዓለም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ግን በቤተ ክርስቲያንና በዓለም መካከል ያለው ልዩነት እየተድበሰበሰ ነው። እንዲያውም ለሰዎች የምንላቸው « ጥሩና የከበረ ሕይወት እስከኖርክ ድረስ፥ የቤተ ክርስቲያን አባል መሆንና ራስህን ክርስቲያን ብለህ መጥራት ትችላለህ።የግዴታ ከሌሎች ሰዎች የተለየህ መሆን የለብህም።» ዛሬ የብዙዎቻችን ሕይወት ይህ አይደለምን? ዛሬ እኛ በዓለም አደባባይ በቅድስናችን ለእግዚአብሔር ምስክሮች ነን? ያለነውር ነው የምንመላለሰው? አይመስለኝም። 

ክርስቶስ አባቱን ያለው ምንድነው? «እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው።ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም።እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።» ዮሐንስ 17፥14-16። ቤተ ክርስቲያን ከዓለም እንድትወጣ አይደለም የለመነው፤ እኛም ዛሬ የምንነጋገረው ከዓለም እንድንለይ፥ የሆነ ነገር ዙሪያችንን አጥረን ከዚህ ዓለም ተደብቀን እንድንኖር አይደለም። ነገር ግን ከዓለም ክፋት የተጠበቅን እንድንሆን ነው። ከዓለም ክፋት ተለይተን በቅድስና በእግዚአብሔር ፊት የምንመላለስ።

ያለነውር መኖር ማለት፥ በቅድስና መኖር ማለት ማናቸውንም የሕይወታችንን አቅጣጫ ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት ነው። እሁድ ጠዋትን ብቻ ወይም በዓላትን ብቻ ሳይሆን ማናቸውንም የሕይወታችንን አቅጣጫ። ልጆች ስናሳድግ ለእግዚአብሔር ክብር ማሳደግ። የትዳር ሕይወትን ስንመራ ለእግዚአብሔር ክብር መምራት። ሥራችንን ስንሰራ ለእግዚአብሔር ክብር መሥራት። ማናቸውንም ሥራ ቢሆን እጅግ ክቡርን የሆነውን ማቅርብ። አለቃችን ማንም ይሁን ማንም፥ ደመወዛችን ምንም ይሁን ምንም ለእግዚአብሔር ክብር መሥራት። ትምህርታችንን ለእግዚአብሔር ክብር መማር ነው። ያለነውር መኖር ማለት ይህ ነው። 


ታላቁ የነፃነት መሪ ማርቲን ሉተር ኪንግ የባርነት ቀንበር ተጭኖት ለነበረው የጥቁር አሜሪካ ሕዝብ ያለው ይህን ነው። የመከራችሁ ቀንበር ስለበዛ ግድ የለም እንደምንም እንደምንም አድርጋችሁ ኑሩ አይደለም ያለው። ያለውን ልንገራችሁ « ከእናንተ መንገድ ለመጥረግ የተጠራ ቢኖር፥ መንገዱን ሲጠር ፥ ማይክል አንጄሎ እንደሚስል፥ ቤትሆቨን ሙዚቃውን እንደሚያቀናብር፥ ሼክሲፒር ቅኔውን እንደሚደርስ፥ አድርጎ ይጥረግ። የሰማይ ሠራዊት ቆም ብለው « ሥራውን በሚገባ የፈጸመ ታላቅ መንገድ ጠራጊ በዚህ ኖሮ ነበር» ብለው እስኪናገሩ ድረስ መንገድ ጠረጋውን በሚገባ መፈጸም አለበት።» ነውር የሌለበት ሕይወት ይሉሃል ይህ ነው። እግዚአብሔር በሰጠን በማንኛውም የሕይወት ጎዳና ለእግዚአብሔር ክብር መኖር። ከዚህ የበለጠ በቅድስናና ያለነውር መኖር የለም። 

Tuesday, October 21, 2014

እግዚአብሔር በክርስቶስ መረጠን

Read in PDF

እግዚአብሔር በክርስቶስ መረጠን ። 
ኤፌሶን 1፥4 
ሐዋርያው በዚህ በዛሬው ዕለት በምንመለከተው ክፍል የሚያነሳው ዋና አሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኛቸው አስደናቂ መለኮታዊ ክንውኖች መካከል ዋና የሆነውን ነገር ነው። እርሱም እግዚአብሔር እኛን የመረጠበት መንገድ ነው።  ምርጫ እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን ቸርነት የምንመለከትበት እይታ እንጂ ደረቅ ስሌት አይደለም።  እኛን መርጦናል እነእገሌን አልመረጠም ብለን በትምክህት የምንጎራደድበት አይደለም።  ክርስቲያኖች የሆንን እኛ ሕይወታችንን ስንመለከት፥ እግዚአብሔር ያደረገልንን ቸርነት ስንረዳ ሕይወታችን  ሁሉ በጥልቅ አምልኮ ይመላል። ምክንያቱም የተደረገልን ሁሉ ከእኛ እንዳልሆነ እናውቃለንና። ከሌሎች የማንሻል ስንሆን አምላካችን ቸርነቱን ለምን አበዛልን? በምንስ ምክንያት ጠራን ስንል መልሱ እርሱ ስለወደደን፥ ስለመረጠን ነው የሚል ነው። በመሆኑም እግዚአብሔር ይህን አደረገ። እግዚአብሔር አሰበን፥ እግዚአብሔር ጎበኘን እንላለን።  

በዘዳግም 7፥6 ላይ ሙሴ ለእስራኤላውያን ያላቸው ይህን ነበር። «ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መረጠህ።እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ስለ በዛችሁ አይደለም እናንተ ከአሕዛብ ሁሉ በቍጥር ጥቂቶች ነበራችሁና» ሙሴ ለወገኖቹ እያለ ያለው፥ የእኛን ሁኔታ ስመለከተው አሁን ለበቃንበት ሁኔታ ያለኝ መግለጫ አንድ ብቻ ነው። እርሱም የእግዚአብሔር ምርጫ ወይም የእግዚአብሔር ፍቅር ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ «እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብም በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ እንዲሰጣችሁ፥ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።» በማለት ተናግሮአል።  ዮሐንስ 15፥16። 

እግዚአብሔር እኛን መምረጡን ማሰብ ለምን ይጠቅማል ስንል መልሱ የክርስትናን ሕይወት ሁሉ የሚዳስስ ነው። በእግዚአብሔር መመረጣችንን ስናስተውል፥ የሰው ትምክህት ስፍራ ያጣል። ድካማችንን በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጠን በእግዚአብሔር ላይ ማረፍ እንጀምራለን። የምንደገፈው በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ይሆናል። ምክንያቱም ከመጀመሪያውም በዚህ ጸጋ ወደ መንግሥቱ እንደተጠራን ተገንዝበናልና። በእግዚአብሔር ላይ ያለን እምነት የጸና ይሆናል። በዚህ ዓለም ጣጣ ከመባከን እግዚአብሔርን በማመስገን መኖር እንጀምራለን።  ለመሆኑ እግዚአብሔር መቼ መረጠን? ለምንስ መረጠን? የምርጫውስ ግቡ ምንድነው? 


ዓለም ሳይፈጠር መረጠን 
ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።

እግዚአብሔር እኛን የመረጠን ዓለም ሳይፈጠር ነው፤ ይህ ዓለም ሳይፈጠር የሚለው ቃል እግዚአብሔር ስለእኛ ማሰብ የጀመረው፥ የእኛን የመዳን መንገድ ማዘጋጀት የጀመረው፥ እኛን ከመፍጠሩ በፊት፥ ዓለምን ሳይመሠርት በፊት እንደሆነ የሚያመለክት ነው። መዳናችን ሙሉ በሙሉ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። (ኤፌ 2፥8፡9) እንደእውነቱ ከሆነ ይህ የእግዚአብሔር ምርጫ የእኛን ማዳን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም ሃሎ እግዚአብሔር በመንግሥቱ፤ ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር በመንግሥቱ ነበረ» በማለት አባቶቻችን በቅዳሴያቸው እንዳመሰገኑት እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር በክብሩ በሥልጣኑ፥ በመንግሥቱ ያለ አምላክ ነው። እኛን የፈጠረው ረዳት ሽቶ አይደለም። ወደፊት በሰፊው እንደምናየው እኛን መፍጠሩ እንኳ ከፍቅሩ የተነሣ ነው።  

እግዚአብሔር ሳይሆን ቀድሞ፥ ከዘመን በፊት አስቀድሞ ለእርሱ የሚሆኑትን እንደሚመርጥ፥ ለአገልግሎት እንደሚጠራ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን በነበሩት የእግዚአብሔር አገልጋዮች ሕይወት ውስጥ እናየዋለን። ኤርምያስን «የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።በሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፥ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።።» ነበር ያለው። ኤር 1፥4፡5። ቅዱስ ጳውሎስም ለገላትያ ክርስቲያኖች ስለ ሕይወት ታሪኩ ሲተርክ እግዚአብሔርን «በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር» በማለት ነበር የጠራው። ገላ 1፥15። ሐዋርያው እያለ ያለው ከእናቱ ማኅፀን ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንከን የለሽ እንደመራ አይደለም። ነገር ግን እያንዳንዱን የሕይወቱን ክንውን የሚያውቅ አምላክ ጳውሎስን አስቀድሞ ማወቁን፥ በኃጢአት እያለ እንኳ፥ በእግዚአብሔር የተወደደ መሆኑን ነው።  ልበ አምላክ ዳዊትም  «እኔ በስውር በተሠራሁ ጊዜ፥ አካሌም በምድር ታች በተሠራ ጊዜ አጥንቶቼ ከአንተ አልተሰወሩም።ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይኖር በመጽሐፍህ ተጻፉ።» በማለት እግዚአብሔር የወደደው ያፈቀረው፥ በቸርነቱ ያሰበው ገና በእናቱ ማኅፀን ሳይሠራ እንደሆነ ገልጦአል።  መዝ 138፥15፡16። 


ብዙውን ጊዜ ስለማንነታችን ስናስብ ይህን ታላቅና ዘላለማዊ የሆነውን የእግዚአብሔርን እቅድ ማሰብ ይኖርብናል። ዓለም ሳይፈጠር የመረጠንን አምላክ ስናስብ፥ የዛሬው ጉድለታችን፥ ውድቀታችን፥ ማግኘትችን ይሁን ማጣታችን ማንነታችንን እንደማይወስነው እንገነዘባለን። ሰዎች ስለእኛ የሚናገሩት በዛሬው ማንነታችን ላይ ተመሥርተው ነው። እግዚአብሔር ግን ስለእኛ የሚናገረው ዓለም ሳይፈጠር ባዘጋጀልን ዘላለማዊ ዕቅድ ላይ ሆኖ ነው፥ ክብርና ምስጋና ለዚህ የፍቅር ጌታ ይሁን። አሜን።