Friday, October 24, 2014

በክርስቶስ መረጠን

Read in PDF

 በክርስቶስ መረጠን። 
« ዓለም ሳይፈጠር፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን።» ኤፌሶን 1፥4 ይህ እግዚአብሔር እኛን የመረጠበት ጸጋ የተከናወነው በክርስቶስ ነው። እግዚአብሔር አስቀድሞ ሲፈጥረን በእርሱ አርዓያና አምሳል ነበር። (ዘፍ 1፥27) ሆኖም ግን በአንዱ በአዳም በደል ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ሲገባ፥ በሰው ላይ የነበረውን የእግዚአብሔርን አርዓያና አምሳል አደበዘዘው፥ አጎደፈው፥ አበላሸው። ወደፊት በኤፌሶን ምዕራፍ ሁለት ጥናታችን በሰፊው እንደምናየው ሰው በእግዚአብሔር ቍጣ ሥር ወደቀ። ይህ የሰው ውድቀት ከእግዚአብሔር የተሰወረ ነውን? እግዚአብሔር የማያውቀው ነውን? አይደለም። እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት ወይ ዓለም ሳይፈጠር የሰውን ድካምና ውድቀት ያውቅ ነበር። ሰው በድካሙ ከገባበት ውድቀት የሚድንበትንም መንገድ አዘጋጀ። በመሆኑም በአንዱ ሰው የገባውን ሞት ድል ያደርገው ዘንድ አንዱን ልጁን ዓለምን ለማዳን ላከው። በሥላሴ ምክር የተዘጋጀው የመዳን መንገድ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው በክርስቶስ መረጠን ሲል እግዚአብሔር እኛን የእርሱ ሊያደርገን ያዘጋጀው መንገድ ክርስቶስ መሆኑን ለማመልከት ነው። 

የወልድ እግዚአብሔር ሰው መሆን አዳም ከወደቀ በኋላ የታቀደና የተወሰነ አይደለም፤ዓለም ሳይፈጠር የተወሰነ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ስብከቱ ላይ ግልጥ እንዳደረገው፥ ልክ እንደእኛ ምርጫ ፥የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ሞትና ትንሣኤ ዓለም ሳይፈጠር በእግዚአብሔር የታቀደ እና የተወሰነ ነው። ሐዋርያው በዚያ ለተሰበሰቡ በሺ ለሚቆጠሩ ሰዎች ያለው ይህን ነው። «የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት።እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፥ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና።» ሐዋ 2፥22-24 ። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው፥ ክርስቶስ ለእኛ መዳን መሥዋዕት እንዲሆን ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ የተዘጋጀ መሆኑን ነው። 


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ 17 በሚገኘውና ስለእኛ በጸለየው የሊቀ ካህነቱ ጸሎት ላይ ስለዚህ እውነት በመደጋገም ይናገራል። « እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤ . . .እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው። . . .አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።»  

ይህ በጥልቅ ምስጋና ውስጥ እንድንሆን የሚያደርግ ነው። ተመርጠናል። ዓለም ሳይፈጠር ተመርጠናል። ቅዱሳንና ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ ተመርጠናል። በፍቅር እንሆን ዘንድ ተመርጠናል። በክርስቶስ ተመርጠናል። አብ ለወልድ ሰጥቶናል። ወልድ ደግሞ በዘላለም ፍቅሩ ይዞናል። ሞቶልናል። አክብሮናል።  ሕይወት ሰጥቶናል። 

ስለሆነም በጀመርነው መንፈስ ትምህርታችንን እንደምድም፤ « እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናነተ አይደላችሁም፤ እኔ ጠራኋችሁ እንጂ እናንተ አይደላችሁም»  አለ፤ ለምንድነው ሐዋርያቱን እንዲህ ያለው፥ እንዲህ ያላቸው ሊያጽናናቸው ነው። ያላቸው፥ ድካማችሁን አውቀዋለሁ፥ ችግራችሁን አውቀዋለሁ፥ ይህንን አውቄ ነው የጠራኋቸው ሲል ነው። መርጦ የሚጸጸት አይደለም። በዚህ በአሜሪካ በየዘመኑ ምርጫ ይደረጋል። ታዲያ ጥሎባቸው አንዱን ወደ ስልጣን ካወጡት በኋላ ብዙም ሳይቆይ በምኑም በምኑም መክሰስ ይጀምራሉ። ያን የፖለቲካ ተንታኞች « የገበያተኞች ጸጸት ( buyers remorse) » ይሉታል። መርጠው ይጸጸታሉ። ይህ የሰው ድርጊት ነው። 


አምላካችን ግን የመረጠን፥ ሕይወቱን ለእኛ የሰጠን ድካማችንን አውቆ ነው። እንዲያውም « እናንት ደካሞች ወደእኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ነው ያለን። በመስቀል ላይ ሆኖም « አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው ነው ያለው። ዛሬ ታዲያ ይህን ድካማችንን እያወቀ የጠራንን ጌታ፥ ድካማችንን ከእርሱ ለመሸሸግ መድከም የለብንም፤ በድካማችን የሚራራልን አምላክ ስላለን ደፍረን ወደ እርሱ እንምጣ በፍቅሩ የመረጠንንን፥ ለቅድስና የጠራንን፥ በልጁ የወደንን ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር፥ እርሱን ደስ ካሰኙት ቅዱሳኑ ጋር ሆነን፥ እናክብረው፥ እናወድሰው እናመስግነው እንስገድለት።አሜን። 

No comments:

Post a Comment